በጥቃቱ አራት ህጻናትን ጨምሮ 133 ሰዎች ሲገደሉ እና 150 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል
ሩሲያ ብሔራዊ የሀዘን ቀን አወጀች።
ሩሲያ ከሞስኮ በቅርብ ርቀት ላይ በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ በተቃጣው ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ለማስብ ብሔራዊ የሀዘን ቀን በማወጅ ሰንደቅአላማዋን ዝቅ አድርጋ እያውለበለበች ነው።
ይህ ጥቃት ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ በሩሲያ ውስጥ የተከሰተ እጅግ ከባዱ ነው ተብሏል።
አራት ህጻናትን ጨምሮ 133 ሰዎች እንዲገደሉ እና ለ150 ሰዎች እንዲቆስሉ ምክንያት ከሆነው ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉትን እንደሚያድኑ እና እንደሚቀጡ የዛቱት ፕሬዝደንት ፑቲን የሀዘን ቀን አውጀዋል።
ፑቲን ጥቃቱን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው "ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መጽናናትን ከልቤ እመኛለሁ"ብለዋል።
"መላ ሀገሪቱ እና መላው ህዝብ ከእናንተ ጋር እያዘነ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል ፑቲን።
ለጥቃቱ እስላሚክ ስቴት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቢገልጽም፣ ፑቲን ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ነበር ካሏቸው አጥቂዎች ጋር ግንኙነት ያለውን ታጣቂ ቡድን ስም በይፋ አልጠቀሱም።
ፑቲን በዩክሬን በኩል መንገድ ከፍተው አጥቂዎቹን ለማስወጣት የሞከሩ ነበሩ ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን "አለምአቀፍ ሽብር" ሲሉ በጠሩት በዚህ ጥቃት ዩክሬን ተሳትፎ የለኝም ስትል አስተባብላለች።
ሰዎች ባለፈው አርብ እለት አራት ታጣቂዎች ገብተው ግድያ በፈጸሙበት 6200 መቀመጫ ባለው የክሮከስ ሲቲ አዳራሽ የአበባ ጉንጉን እያስቀመጡ ናቸው።