ሩሲያ ጥቃቱን የሽብር ጥቃት ነው ያለች ሲሆን፣ ዓለም ሊያወግዘው ይገባል ብላለች
በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ ላይ ታጣቂዎች ማምሻውን ባደረሱት ጥቃት 40 ሰዎች ተገደሉ።
ታጣቂዎቹ በአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ እና በቦምብ ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በሞስኮ በሚገኘው ኮርኩስ ሲቲ ሆል አዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ በነበረ የሙዚቃ ድግስ ላይ መሆኑን የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ አስነብቧል።
መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ወደ አዳራሹ በማቅናት የሙዚቃ ድግሱን በመታደም ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ድንገት ተኩስ በመክፈት ጉዳት ማድረሳቸውም ነው የተገለጸው።
ታጣቂዎቹ በአዳራሹ ከፍተኛ እሳት እንዲነሳ የእጅ ቦምብን ጨምሮ ሌሎች ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን መወርወራቸውንም የአይን እማኞች ተናግረዋል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ባወጡት መረጃ ጥቃቱን ያደረሱት የጥይት መከላከያ ጃኬት የለበሱ አምስት ሰዎች እንደሆኑ አስታውቀዋል።
የመሳሪያ ተኩሱ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ያክል የቀጠለ ሲሆን፣ በኮንሰርቱ አዳራሽ ውስጥ የነበሩ ሰዎችም ራሳቸውን ለማዳን ለረጅም ደቂቃ መሬት ላይ ተኝተው ነበር ነው የተባለው።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ፣ ፕሬዝዳንት ሺላድሚር ፑቲን ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የሩሲያ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ በሙዚቃ ድግስ ላይ የተፈጸመው ድርጊት የሽብር ተግባር ነው ሲል አውግዟል።
የሩሲያ የደህንነት ምክር ቤት ሓላፊ ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው፣ ይህንን ያደረጉት ዩክሬናውያን ናቸው፣ ለዚህም የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ ዝተዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማፊያ ዛራኮቫ በበኩላቸው፣ ይህንን አረመኔያዊ ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል።