የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ለይፋዊ ጉብኝት ሰሜን ኮሪያ ገቡ
ከ10 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬኑ ጦርነት መሳተፍ ጀምረዋል በተባለበት ወቅት ነው ሚኒስትሩ ፒዮንግያንግ የገቡት
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ከዩክሬን የቀረበላትን የጦር መሳርያ እርዳታ ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች
የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር አንድሬ ቤሉሶቭ ለይፋዊ ጉብኝት ሰሜን ኮሪያ ገቡ።
ሚኒስትሩ ሲገቡ የሰሜን ኮሪያ አቻቸው ክዋንግ ቾል አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ በቆይታቸው ከሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ቤሉሶቭ የሚመክሩባቸው ጉዳዮች ግን እስካሁን በዝርዝር አልተጠቀሱም።
ሰሜን ኮሪያ በኒዩክሌር ፕሮግራሟ፤ ሩሲያ ደግሞ በዩክሬን በከፈተችው ጦርነት ምክንያት በመንግስታቱ ድርጅት በርካታ ማዕቀቦች ተጥሎባቸዋል።
ሀገራቱ ማዕቀቦቹን በጋራ ለማለፍ በሰኔ ወር 2024 የስትራቴጂካዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ አንዱ ሀገር ጥቃት ሲደርስበት ሌላኛው ፈጣን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርግ በሌላ አገላለጽ "ጠላትሽ ጠላቴ ነው" የሚል መርህ ያለው ነው።
በዚህም ፒዮንግያንግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ሞስኮ መላኳን ምዕራባውያን ሲገልጹ ቆይተዋል።
በቅርቡም ከ10 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ሩሲያ ገብተው በዩክሬኑ ጦርነት እየተሳተፉ መጀመራቸውን ዋሽንግተን ፖስት መዘገቡ ይታወሳል።
ኬቭ አሀዙን ወደ 12 ሺህ ያስጠጋችው ሲሆን የፒዮንግያንግ ወታደሮች ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ዘልቆ ከገባው የዩክሬን ጦር ጋር እየተዋጉ መሆኑን ገልጻለች።
ዩክሬን የብሪታንያውን ስቶርሚ ሻዶው ሚሳኤል ወደ ሩሲያ ስትተኩስ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችም መቁሰላቸውን ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣችው መግለጫ ጠቁማለች።
ሩሲያም ሆነች ሰሜን ኮሪያ በወታደሮቹ ስምሪት ዙሪያ ማረጋገጫ ባይሰጡም የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ሩሲያ የዩክሬኑን ጦርነት እስክታሸንፍ ድረስ እንደግፋታለን" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል የሰሜን ኮሪያ ጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ከዩክሬን የቀረበላትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጥያቄ በጊዜያዊነት ውድቅ ማድረጓ ተዘግቧል።
በዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር የተመራ ልዑካን ቡድን ከሰሞኑ በሴኡል ተገኝቶ የጦር መሳርያ እርዳታ ጥያቄ ቢያቀርብም ደቡብ ኮሪያ ለጥያቄ ምላሽ የምሰጠው በሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ የወደፊት ዕርምጃ ላይ በመመስረት ነው ብላለች።
ከሩሲያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለማግኘትና ጦራቸው በሚገባ እንዲሰለጥን የሚሹት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያ ጋር ትብብራቸውን ለማሳደግ በጽኑ መፈለጋቸው ገለልተኛ አቋም የነበራትን ሴኡል ወደ ዩክሬኑ ጦርነት ሊያስገባት እንደሚችል ተገምቷል።