ደቡብ ኮርያ ከዩክሬን የቀረበላትን የጦር መሳርያ እርዳታ ጥያቄ ውድቅ አደረገች
በዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር የተመራ ልዑካን ቡድን በሴኡል ተገኝቶ የጦር መሳርያ እርዳታ ጥያቄ አቅርቧል
ደቡብ ኮርያ በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ የምሰጠው ምላሽ የሰሜን ኮርያን ድርጊት መሰረት ያደረገ ብቻ ነው ብላለች
ደቡብ ኮርያ ለዩክሬን ቀጥተኛ የጦር መሳርያ ድጋፍ ከማድረግ መቆጠቧን እንደምትቀጥል አስታወቀች ፡፡
ሰሜን ኮርያ ወደ ሩስያ ወታደሮቿን ከላከች ጀምሮ ሴኡል ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግ ከአጋሮቿ እና ከኬቭ መሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበላት ቢሆነም ሀገሪቷ ገለልተኛ መሆንን መርጣለች፡፡
በትላንትናው እለት ወደ ደቡብ ኮርያ ያቀኑት የዩክሬን ልዑካንም ይህንኑ የጦር መሳርያ ድጋፍ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት አጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ቀጥተኛ የጦር መሳርያ ድጋፍ እንደማታደረግ ያስታወቀችው ሴኡል በሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ የወደፊት ዕርምጃ ላይ በመመስረት እንዲህ ዓይነቱን ዕርዳታ ግምት ውስጥ ልታስገባ እንደምትችል ተናግራለች።
በዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ የተመራው ልዑካን ቡድን ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ሁለቱም ወገኖች ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ የምትልከውን ጦር እንዲሁም የቴክኖሎጂ እና የጦር መሳሪያ ልውውጥን በተመለከተ መረጃ መለዋወጥን ለመቀጠል ተስማምተዋል ሲል የፕሬዝዳንቱ ቢሮ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የልዑካን ቡድኑ በተጨማሪም የሴኡል የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሺን ዎንሲክ እና የመከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ-ህዩንን አግኝተው በሴኡልና በኬቭ መካከል ስላለው ትብብር ተወያይተዋል።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በጥቅምት ወር ከደቡብ ኮሪያ ብሮድካስት ኬቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዩክሬን ለሴኡል የጦር መሳሪያ ድጋፍ እና የአየር መቃወሚያዎችን ጨምሮ ዝርዝር የጦር መሳርያ ድጋፍ አይነቶችን ጥያቄ ለመላክ አቅዳለች ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ዲፕሎማት ለሮይተርስ እንደተናገሩት በሁለቱ ሀገራት መካከል በዝግ በር የተደረጉ ውይይቶች የጦር አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ለመምታት የሚያስችሉ የአየር መከላከያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮሩ ቢሆንም በዚህ ወር በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፍ ደቡብ ኮርያ ድጋፍ በማድረጓ ላይ እርግጠኛ እንዳትሆን አድርጓል፡፡
አብዛኞቹ ደቡብ ኮሪያውያን በፒዮንግያንግ እና በሞስኮ መካከል እያደገ የመጣውን ወታደራዊ ግንኙነት እንደ ስጋት ይመለከቱታል፡፡
ነገር ግን ጋሉፕ በኮሪያ ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት 82 በመቶ ዜጎች ለዩክሬን የጦር መሳሪያን ጨምሮ ወታደራዊ እርዳታ መላክን ተቃውመዋል።
ተንታኞች የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ዙርያ በሀገር ውስጥ ያለባቸው ተቃውሞ ከፍተኛ በሆነበት እንዲሁም በጦር መሳርያ ድጋፉ የተነሳ ከሚቀጥለው የአሜሪካ መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ሊበላሽ በሚችልበት ሁኔታ ድጋፍ ማድረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ፡፡