የሩሲያ ሚሳኤሎች ምዕራባውያን ለዩክሬን ከላኳቸው እጅግ የላቀ አቅም አላቸው - ፑቲን
ፕሬዝዳንቱ "ምዕራባውያን ተቀናቃኞቻችን ምን ያህል ወሳኝ መሳሪያዎች እንዳላቸውና የት እንደሚገኙ እናውቃለን"ም ሲሉ ተናግረዋል
የጋራ ደህንነት ስምምነት ድርጅት (ሲኤስቲኦ) በካዛኪስታን መዲና አስታና ጉባኤውን እያካሄደ ነው
የሩሲያ ጦር ምዕራባውያን ለዩክሬን ከላኳቸው እጅግ የላቀ አቅም ያላቸው ሚሳኤሎችን ታጥቋል አሉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን።
ፕሬዝዳንቱ ዋሽንግተን እና ሌሎች ምዕራባውያን የኬቭ አጋሮች የላኳቸው ሚሳኤሎች በአውደ ውጊያው ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንደሌላቸውም አብራርተዋል።
የጋራ ደህንነት ስምምነት ድርጅት (ሲኤስቲኦ) ጉባኤ በካዛኪስታን መዲና አስታና ሲካሄድ ነው የሞስኮ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ከአሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ሰራሾቹ እንደሚልቁ የተናገሩት።
ፑቲን የሩሲያው "እስክንድር" የአጭር ርቀት ሚሳኤል ባይደን ዩክሬን ወደ ሩሲያ ምድር ዘልቃ ጥቃት እንድትፈጽምበት ከፈቀዱላት ሚሳኤል "ኤቲኤሲኤምሲ" ጋር ተመሳሳይ የመሸከም አቅም እንዳለውና ረጅም ርቀት በመምዘግዘግ ግን የተሻለ መሆኑን አንስተዋል።
በ2023 ይፋ የተደረገውና "ኤቲኤሲኤምሲ"ን ይተካል የተባለው "ፒኤርኤስኤም" የአጭር ርቀት ሚሳኤልም ከሩሲያ አቻዎቹ እንደማይበልጥ መናገራቸውን አርቲ አስነብቧል።
አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በያዝነው ህዳር ወር መጀመሪያ ለዩክሬን የላኳቸው ሚሳኤሎች ሩሲያን ለማጥቃት እንዲውሉ መፍቀዳቸው ይታወሳል።
ኬቭም የሀገራቱን ሚሳኤሎች መተኮሷን ተከትሎ ሞስኮ "ኦሬሽኔክ" የተሰኘ መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ዩክሬኗ ዲኒፕሮ ማስወንጨፏ አይዘነጋም።
በጥር ወር ከዋይትሃውስ የሚወጡት ባይደን ለኬቭ ፈቃድ መስጠታቸው የኒዩክሌር ጦርነት ያስነሳል ያሉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለምዕራባውያን የማስጠንቀቂያ መልዕክታቸውን ማስተላለፍ ቀጥለዋል።
በአስታናው ጉባኤም "ምዕራባውያን ተቀናቃኞቻችን ምን ያህል ወሳኝ መሳሪያዎች እንዳላቸው፣ የት እንደሚገኙ እና ለዩክሬን ምን ያህል መሳሪያዎች እንደላኩና ለመላክ እንዳቀዱ ጠንቅቀን እናውቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ምዕራባውያን ምንም ያህል ዘመናዊ መሳሪያዎችን ለዩክሬን ቢልኩ ሶስተኛ አመቱን ሊይዝ በተቃረበው ጦርነት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድርም ጠቅሰዋል።
በወሳኝ የሚሳኤል ስርአት ምርት ሞስኮ ከኔቶ አባል ሀገራት በ10 እጥፍ እንደምትልቅና በቀጣዩ አመቱ ከአለም ከ25 እስከ 30 በመቶውን ድርሻ እንደምትይዝም ነው የጠቆሙት።
ፕሬዝዳንት ፑቲን "ሩሲያ የታጠቀቻቸው ካሊበር ክሩዝ ሚሳኤሎች፣ ኪንዝሃል እና ዚርኮን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች በአለም የሚወዳደራቸው የለም" ሲሉም አብራርተዋል።
ሞስኮ በቀጣዩ አመት በአለማችን ወደር የማይገኝለትን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ይኖራታልም ነው ያሉት።