ሩሲያ በዩክሬን ተኩስ ለማቆም ለአሜሪካ ያቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተደራዳሪ ቡድናቸውን ወደ ሞስኮ መላካቸው ተሰምቷል

አሜሪካ እና ዩክሬን በሳኡዲ ባደረጉት ምክክር ኬቭ ለ30 ቀናት ተኩስ ለማቆም መስማማቷ ይታወሳል
ሩሲያ ሶስት አመታት ያስቆጠረውን የዩክሬን ጦርነት ለማቆም ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለአሜሪካ ማቅረቧ ተነገረ።
ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ክሬምሊን ከዚህ ቀድም ሲያቀርባቸው የነበሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ሀገራቱን ለማሸማገል እየሞከረች ለምትገኘው ዋሽንግተን ልኳል።
ሩሲያ የጦርነቱ ዋነኛ ምክንያት አድርጋ የምታነሳው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋትና የዩክሬን የድርጅቱ አባልነት ጉዳይ መቆምን ከዋሽንግተን መተማመኛ ፈልጋለች።
የውጭ ሀገራት ወታደሮችን በዩክሬን የማሰማራት ሃሳብም ውድቅ ይደረግ ዘንድ መጠየቋን የሬውተርስ ምንጮች ዘግበዋል።
አለማቀፉ ማህበረሰብ ክሬሚያን ጨምሮ አራት የዩክሬን ግዛቶች (ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ኬርሰን እና ዛፓሮዥያ) የሩሲያ ሉአላዊ ግዛት አካል መሆናቸውን እውቅና እንዲሰጡም ይጠይቃል ለአሜሪካ የቀረበው ሰነድ።
በሳኡዲ አረቢያ ጂዳ በተካሄደው የአሜሪካ እና ዩክሬን ባለስልጣናት ተጠባቂ ምክክር ዩክሬን ለ30 ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ መስማማቷን ማሳወቋ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጊዜያዊ ተኩስ አቁሙ ከሩሲያ ጋር ዘላቂ የሰላም ስምምነት ለመድረስ መነሻ ይሆናል በሚል ድጋፍ መስጠታቸውም አይዘነጋም።
በምርጫ ቅስቀሳቸው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን "በአንድ ቀን አስቆመዋለው" ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደራዳሪ ልኡካቸውን ወደ ሞስኮ መላካቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማርኮ ሩቢዮ "አሁን ኳሱ በሩሲያ ሜዳ ነው" በማለት የሞስኮ ምላሽ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ሩሲያ በድጋሚ አቅርባቸዋለች የተባሉት ቅድመ ሁኔታዎች በተመለከተ በአሜሪካ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲም ሆነ ዋይትሃውስ አስተያየት አልሰጡም።
ለጦርነቱ መቀስቀስ ዩክሬንን ተጠያቂ በማድረግ ለሩሲያ የተለሳለሰ አቋም አሳይቷል በሚል የሚወቀሰው የትራምፕ አስተዳደር ሞስኮ ከምታቀርባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለተወሰኑት ድጋፍ ሲሰጥ ተደምጧል።
ሩሲያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከአሜሪካ ጋር ባደረገቻቸው ድርድሮች ላይ የቀረቡ ሃሳቦች አሁንም ተደግመዋል የሚሉ ተንታኞች፥ የአሜሪካ በአውሮፓ ምድር ወታደራዊ አቅም መጠናከርን በፍጹም እንደማትፈቅድ አቋሟን በግልጽ ማሳየቷን ይናገራሉ።
በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ያለችውን ጦርነት ስትጀምርም ለባይደን አስተዳደር ሶስት ቅድመ ሁኔታውችን አስቀምጣ እንደነበር ሬውተርስ አገኘውት ያለው ሰነድ ያመላክታል።
የመጀመሪያው የአሜሪካ እና ኔቶ ሃይሎች በአዳዲሶቹ የኔቶ አባል ሀገራት ወታደራዊ ልምምድ እንዳያደርጉ የሚል ነው።
አሜሪካ የሩሲያን ግዛት ተሻግሮ ጥቃት ማድረስ የሚችል መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ወደ አውሮፓ ሀገራት እንዳትልክ የሚለውም ተካቷል።
አሜሪካ እና ኔቶ በመካከለኛው እስያ እና ካውካሰስ (አርመኒያ፣ አዘርባጃን እና ጆርጂያ) አካባቢ ወታደራዊ ልምምድ እንዳያደርጉ ተጠይቆ የባይደን አስተዳደር ባለመስማማቱ ጦርነቱ መቀጠሉ ይታወሳል።
የትራምፕ አስተዳደርስ ለክሬምሊን ቅድመ ሁኔታዎች በጎ ምላሽ ይሰጣል ወይ የሚለው ተጠባቂ ነው።