አይሲሲ በቀድሞው የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ላይ ያወጣው የእስር ማዘዣ ምን አካቷል?
ሮደሪጎ ዱቴርቴ በዘ ሄግ የሚቀርቡ የመጀመሪያው የእስያ የቀድሞ የሀገር መሪ ሆነዋል

ዱቴርቴ በስልጣን ዘመናቸው በአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ላይ ባወጁት "ጦርነት" በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል
የፊሊፒንስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት (አይሲሲ) የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የ79 አመቱ ዱቴርቴ ከሆንግ ኮንግ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በማኒላ አውሮፕላን ማረፊያ ነው የተያዙት።
የዱቴርቴ ልጅና ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳራ ዱቴርቴ አባታቸው "በሃይል ወደ ዘ ሄግ" መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ዱቴርቴ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ተከሰው በመቅረብ የመጀመሪያው የእስያ የቀድሞ የሀገር መሪ ሆነዋል።
የደቡብ ምስራቅ እስያዊቷን ሀገር ከፈረንጆቹ ከ2016 እስከ 2020 የመሩት ሮድሪጎ ዱቴርቴ በአደንዣዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ላይ "ጦርነት" አውጀው በሺዎች የሚቆጠሩ አዘዋዋሪዎች ተገድለዋል።
የዳቫኦ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅትም በጭካኔ የበርካቶች ህይወት እንዲያልፍ አዘዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።
ዱቴርቴ ግን በአይሲሲ የእስር ማዘዣ ምክንያት በቁጥጥር ስር ሲውሉ "ምንድን ነው ጥፋቴ" ሲሉ ተከራክረዋል።
ሬውተርስ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በቀድሞው የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ላይ ያወጣውን ባለ15 ገጽ የእስር ማዘዣ ተምልክቻለሁ ብሏል።
የእስር ማዘዣው ዋና ዋና ጉዳዮች
- አይሲሲ በዱቴርቴ ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣው ከአራት ቀናት በፊት (መጋቢት 7 2025) ነው፤ ማዘዣው የቀድሞው ፕሬዝዳንትን በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ይከሳል።
- ሰነዱ ዳኞች የቀድሞው መሪ "ዳቮ ዴዝ ስኳድ" የተባለ ገዳይ ቡድን መሪ እንደነበሩ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ማስረጃ እንዳገኙ ይጠቀሳል፤ ፕሬዝዳንት ከሆኑም በኋላ ይህን ቡድን ይከታተሉ እንደነበር ያክላል።
- ዱቴርቴ በጥቂቱ 19 አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች በዳቫኦ ከተማ እንዲገደሉ በቀጥታ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፤ ሌሎች 24 ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች ለተገደሉበት ጥቃትም ዳኞች የቀድሞው ፕሬዝዳንት በወንጀል ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አምነዋል
- የእስር ማዘዣው ዱቴርቴ በእጽ አዘዋዋሪዎች እና ወንጀለኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲፈጸመ አጠቃላይ እቅድ ከማዘጋጀት ባለፈው ለገዳይ ቡድኖች የጦር መሳሪያ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበርም ያሳያል።
- የወንጀል ተጠርጣሪዎችን የሚገድሉ የጸጥታ ሃይሎች ያለመከሰስ መብት እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባታቸው የወንጀል መርማሪዎች ስራ ተደናቅፏል ሲልም ይከሳል።
- ፊሊፒንስ በዲቴርቴ የስልጣን ዘመን በ2019 ከአይሲሲ አባልነት በይፋ ብትወጣም የእስር ማዘዣው ማኒላ የፍርድቤቱ አባል እያለች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከት በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ክሱን የማየት ስልጣን አለው።
የፊሊፒንስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳራ ዱቴርቴ ግን በአይሲሲ የወጣው የእስር ማዘዣ "ለሁሉም ፊሊፒናዊ ስድብ ነው" በሚል ተቃውመውታል።