በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ አምስት ባለጸጎች ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስረዋል ተባለ
ኢለን መስክ ብቻ የ148 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶበታል

ባለጸጎቹ ከጥር ወር ጀምሮ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ተገልጿል
በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ አምስት ባለጸጎች ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስረዋል ተባለ።
የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ሕዳር ወር ላይ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ጥር ወር ላይ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ወዳጆቻቸው፣ የሀገራት መሪዎች እና ባለጸጎች በተገኙበት በይፋ በዓለ ሲመታቸው ተከብሯል።
በዚህ በዓል ላይ የተገኙ የዓለማችን ቀዳሚ ባለጸጎች በዝግጅቱ ላይ ከተገኙበት ቀን ጀምሮ ኪሳራ እያስመዘገቡ እንደሆነ ብሉምበርግ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳድር ዋነኛ አካል የሆኑት ኢለን መስክ ብቻ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የ148 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አስመዝግቧል።
እንዲሁም የአማዞን እና የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ባለቤቱ ጄፍ ቤዞስ 29 ቢሊዮን ዶላር እንደከሰረ ተገልጿል።
የአልፋቤቱ ሰርጌይ ብሪን 22 ቢሊዮን ዶላር፣ የሜታ ኩባንያ ባለቤቱ ማርክ ዙከርበርግ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ፈረንሳዊው የፋሺን ኢንዱስትሪ ባለቤት በርናርድ አርናልት ደግሞ አምስት ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ 17 ኩባንያዎች ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የ1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶባቸዋል ተብሏል።
ለባለጸጎቹ የገቢ መቀነስ ምክንያት ከተባሉት ውስጥ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳድር አዳዲስ እርምጃዎች፣ ከሀገራት ጋር የገቡበት የንግድ እና ቀረጥ ውሳኔዎች እና የተወሰኑት ባለጸጎች ከአስተዳድሩ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አድርገዋል መባሉ ዋነኞቹ እንደሆኑ ተገልጿል።