ሩሲያ በከፍተኛ ጀነራሏ ግድያ የጠረጠረችውን ኡዝቤኪስታናዊ በቁጥጥር ስር አዋለች
የ29 አመቱ ወጣት ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭን ከገደለ 100 ሺህ ዶላር ተሰጥቶት ወደ አውሮፓ እንደሚላክ በዩክሬን ቃል ተገብቶለት እንደነበርም አስታውቃለች
ሞስኮ በስመጥሩ ጀነራል ግድያ የተሳተፉ ሁሉ ዋጋቸውን ያገኛሉ ስትል ዝታለች
የሩሲያ የፌደራል የደህንነት ተቋም (ኤፍኤስቢ) ከጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ ግድያ ጋር በተያያዘ የ29 አመት ኡዝቤኪሳታናዊን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች።
የሩሲያ የኒዩክሌር፣ ባይሎጂካል እና ኪሚካል መከላከያ ሃይል መሪ የነበሩት ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ ትናንት ከቤታቸው ሲወጡ ቦምብ ፈንድቶ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
የዩክሬን የደህንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ኪሪሎቭ የተገደሉበትን "ልዩ ዘመቻ" መምራቱን ሬውተርስ የተቋሙን ሰራተኞች ዋቢ አድርጎ ማስነበቡም አይዘነጋም።
"ኤፍኤስቢ" ባወጣው መግለጫ ግድያውን የፈጸመው ስሙ ያልተጠቀሰ ወጣት በዩክሬን የስለላ ሰራተኞች መመልመሉን ገልጿል።
ኡዝቤኪስታናዊው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ሲደረግበት ኪሪሎቭን ከገደለ 100 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚሰጠውና ወደ ሌላ የአውሮፓ ሀገር እንደሚዛወር ቃል ተገብቶለት እንደነበር ተናግሯል።
በዩክሬን ትዕዛዝ መሰረት ሞስኮ እንደገባም በቤት ውስጥ የተዘጋጀ ፈንጂ ተቀብሎ፤ በኤሌክትሪክ በምትሰራ ሞተር አጥምዶት ጀነራል ኪሪሎቭ በሚኖሩበት አፓርታማ እንዳቆማትም ነው መግለጫው የሚያሳየው።
ወጣቱ ሞተሯ ላይ ካሜራ ገጥሞ በተከራየው መኪና በቅርበት ሁኔታውን ሲከታተል መቆየቱና በቀጥታ የሚቀረጸው ምስል ከዩክሬኗ ዲኒፕሮ ከተማ ወደ እጅ ስልኩ ሲደርሰው እንደነበርም ነው የጠቆመው።
ኪሪሎቭ ከቤታቸው እንደወጡም ተጠርጣሪው ቦምቡን አፈንድቶት ለማምለጥ ሞክሮ እንደነበርና በክትትል እንደተደረሰበት የሩሲያ የደህንነት ተቋም ማሳወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሩሲያ ስመጥር ወታደራዊ አመራር ናቸው የሚባልላቸው ኪሪሎቭ ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በራሷ ግዛት ውስጥ የተገደሉባት ከፍተኛ ጀነራል ሆነዋል።
ኬቭ የ54 አመቱ ጀነራል ከመገደላቸው ከአንድ ቀን በፊት (ሰኞ) የተከለከሉ የኬሚካል መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ አዘዋል በሚል በሌሉበት ክስ መስርታባቸው ነበር።
የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት ሩሲያ በኪሪሎቭ የስልጣን ቆይታ ከ4 ሺህ 800 ጊዜ በላይ የኬሚካል መሳሪያዎችን በዩክሬን ተጠቅማለች ሲል ይከሳል።
ሞስኮ ግን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ክምችቷን በ2017 ሙሉ በሙሉ ማውደሟን በመግለጽ ክሱን ውድቅ ታደርጋለች፤ በጀነራሉ ግድያ የተሳተፉ ሁሉ ዋጋቸውን ያገኛሉ ስትልም ዝታለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የመንግታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት አርብ በሚያደርገው ስብሰባ ሞስኮ የኪሪሎቭ ግድያን ታነሳለች ብለዋል።