አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ “ፓትሪዮት ሚሳኤል ስርአት” ልትልክ ነው
ፔንታጎን ዘመናዊውን የአየር መቃወሚያ ጨምሮ 6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና ተተኳሽ ጥይቶች ለመላክ ወስኗል
ዩክሬን የአሜሪካ ድጋፍ መዘግየት ሩሲያ ተጨማሪ የኬቭ መሬቶችን እንድትይዝ ያደርጋታል የሚል ስጋቷን ገልጻለች
አሜሪካ ዘመናዊውን የሚሳኤልና አውሮፕላን መቃወሚያ (ፓትሪዮት ሚሳኤል ስርአት) ወደ ዩክሬን ለመላክ ወስናለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን እንዳስታወቁት፥ ለፓትሪዮት ሚሳኤል ስርአቱን ጨምሮ 6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና ተተኳሾች ወደ ኬቭ በፍጥነት ይላካሉ።
ወታደራዊ ድጋፉ ፕሬዝዳንት ባይደን የፈረሙት የ61 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አካል ነው መባሉንም ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ልድሚር ዜለንስኪ ጸረ ሚሳኤሉ ሩሲያ በአየር የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች ለመመከት “በፍጥነት” ሊደርሰን ይገባል ብለዋል።
የ6 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፉ ከፔንታጎን ሳይሆን ከአሜሪካ የመሳሪያ አምራቾች ተገዝቶ የሚቀርብ መሆኑ ለኬቭ በፍጥነት ላይደርሳት እንደሚችል ነው የተገለጸው።
“የአሜሪካን የድጋፍ ውሳኔ ስንጠብቅ የሩሲያ ጦር ድል እያደረገ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ፥ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ቃል የገቡትን ድጋፍ በፍጥነት እንዲልኩ ጠይቀዋል።
ለኬቭ በሚስጢር ረጅም ርቀት የሚምዘገዘጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን የላከችው ዋሽንግተን እጅግ ዘመናዊና የላቀ አየር መቃወሚያ ነው የሚባልለትን ፓትሪዮት ሚሳኤል ስርዓት ለመላክ ጥድፊያ ውስጥ መሆኗ ተጠቁሟል።
ከምድር ወደ አየር የሚተኩሰው ፓትሪዮት ሚሳኤል እንደ ክሩዝ ሚሳይሎች ያሉ ፈጣን የአየር ላይ ኢላማዎችን እና አውሮፕላኖችን የሚመታ ነው።
የአየር መቃወሚያው ከወደ ሞስኮ የሚተኮሱ ሚሳኤሎችን ለመምታትም ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ነው የተነገረው።
አሜሪካ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ቢሊየን ዶላሮች የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለኬቭ ብትልክም የተፈለገው ውጤት በአጭር ጊዜ ሊመጣ አልቻለም።
ኬቭ ባለፈው አመት እጀምረዋለው ያለችው ግዛቶቿን የማስመለስ መልሶ ማጥቃትም ከጅምሩ መሰናከሉ አይዘነጋም።