የዩክሬን ጦር ከ3 መንደሮች ለቆ ለመውጣት ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ያጸደቀው ባለፈው ሳምንት ነበር
የዩክሬን ጦር በምስራቅ ግንባር ያሉ ሶስት መንደሮችን ለቆ ለመውጣት መገደዱን የዩክሬን ጦር አዛዥ ተናግረዋል
የዩክሬን ጦር፣ በሩሲያ ጦር የቁጥር እና የተተኳሽ ብልጫ ስለተወሰደበት በምስራቅ ግንባር ያሉ ሶስት መንደሮችን ለቆ ለመውጣት መገደዱን የዩክሬን ጦር አዛዥ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
የጦር አዛዡ ጀነራል ኦሌክሳኔደር ሲይርስኪ መግለጫ ኪቭ የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እጇ ከገባ እንደምታረጋጋው የምትገልጸው ግንባር ችግር ውስጥ መግባቱን ያመላክታል።
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ያጸደቀው ባለፈው ሳምንት ነበር።
"በግንባር ያለው ሁኔታ ተባብሷል" ያሉት ሲይርስኪ የተወረረችው ማሪንካ ምዕራብ እና ባለፈው የካቲት በሩሲያ ቁጥጥር ስር የዋለችው አቭዲቪካ ሰሜንምዕራብ ክፍሎች "በከባድ ችግር" ውስጥ ናቸው ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ዩክሬን የሩሲያን እቅድ ለማዛባት የሚያስችላትን የጦር መሳሪያ በፍጥነት እንዲያደርሳት አዲስ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘለንስኪ የፖትሪዎት ሚሳይል ስርአት በተቻለ ፍጥነት እንዲላክላቸው ከአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ማይኖሪቲ መሪ ከሆኑት ሀኬም ጀፍሪስ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት አስምረው መናገራቸውን ገልጸዋል።
ሲርስኪ የኪቭ ወታደሮች ከቤርዲች እና ከሰሜንቪካ በምዕራብ አቅጣጫ እንዲሁም ከአብዲቪካ እና ኖሞቪካሂልቪካ በስተሰሜን በኩል ምሽግ ይዘዋል ብለዋል።
"ጠላት የተወሰነ የታክቲክ ስኬት አግኝቷል። ነገርግን ዘመቻ ለማድረግ የሚያስችል ጠቀሜታ አላገኘም" ያሉት ሲርስኪ ሩሲያ አራት ብርጌዶችን አሰልፋ እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል።
ሲይርስኪ እንዳሉት ሸንፈት የደረሰባቸው ወታደሮች በአዲስ ኃይል ተተክተዋል።
የሩሲያ ወታደሮች አቭዲቪካን ከተቆጣጠሩ በኋላ የዩክሬናውያን የጦር መሳሪያ እጥረት እና ያላቸውን የሰው ኃይል የበላይነት በመጠቀም ቀስበቀስ ወደፊት እየገፉ ይገኛሉ።
ሩሲያ አቭዲቪካን ከያዘች በኋላ በኦችርታይን መንደር አቅጣጫ 15 ኪሎሜትር ወደፊት ገፍታለች ተብሏል።
ሲይርስኪ ቻሲቭ ያር እና በሰሜን ምስራቅ የምትገኘው ኢቫንቪስኬ ከተማ ከፍተኛ ውጊያ የሚካሄድባቸው የግንባር ቀጣናዎች ናቸው ብለዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዩክሬን በቻሲቭ ያር ያደረገችውን የመልሶ ማጥቃት ሙከራ ማክሸፉን ገለጿል።