አሃዙ ሩሲያ ለጦርነቱ የምታወጣውን ወጪ ገልጦ ያሳየ ነው ተብሏል
ሞስኮ በ2023 ለመከላከያ የምታወጣውን ወጪ በእጥፍ አሳድጋ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጭማሪ መወጠኗ ተሰምቷል።
ወጪው ከመንግስት ጠቅላላ ወጪ አንድ ሦስተኛ መሆኑን ሮይተርስ አገኘሁት ባለው የመንግስት ሰነድ ላይ ተመላክቷል።
ይህ አሃዝ ሩሲያ ለጦርነቱ የምታወጣውን ወጪ ገልጦ ያሳየ ነው ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2023 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ብቻ ሩሲያ የጠቅላላ በጀቷን 12 በመቶ ወይም 600 ቢሊዮን ሩብል ለመከላከያ ወጪ አድርጋለች። ይህም ለ2023 ጠቅላላ ከታቀደው 4.98 ትሪሊዮን ሩብል (54 ቢሊዮን ዶላር) የበለጠ ነው።
በ2023 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ የመከላከያ ወጪዎች 5.59 ትሪሊዮን ሩብል ወይም ከጠቅላላው 14.97 ትሪሊዮን ሩብልስ ውስጥ 37 በመቶ መውጣቱን ሰነዱ አሳይቷል።
የሩስያ የበጀት እቅድ 17.1 በመቶው ለ"ብሄራዊ መከላከያ" ተመድቧል።
መንግስት በቁጥሮች ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ሞስኮ በዩክሬን "ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ" ያለችውን ጦርነት ለመደገፍ የምታወጣው ከፍተኛ የመከላከያ ወጪ፤ የበጀት ጉድለቷን የበለጠ ሊያሰፋው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ሮይተርስ ባደረገው ስሌት ሩሲያ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ለ2023 በጠቅላላ ከታቀደው የበጀት ወጪ 19.2 በመቶውን ለመከላከያ ወጪ አድርጋለች።