ሳኡዲ በምታዘጋጀው የዩክሬን የሰላም ጉባኤ ሩሲያ አልተጋበዘችም ተባለ
በቀጣይ ሳምንት በጂዳ በሚደረገው ምክክር ከ30 በላይ ሀገራት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል
መድረኩ ገለልተኛ አቋም የያዙ ሀገራት ለኬቭ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ የሚቀርብበት ነው ተብሏል
ሳኡዲ አረቢያ በዩክሬን ሰላምን ለማስፈን ያለመ አለማቀፍ መድረክ በቀጣዩ ሳምንት ታስተናግዳለች።
በዚህ መድረክም ከ30 በላይ ሀገራት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ብሏል ወልስትሪት ጆርናል ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ግለሰብ በዋቢነት በመጥቀስ።
ግብጽ፣ ዛምቢያ፣ ብራዚል፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ እና ቺሊ በመድረኩ እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ፖላንድ እና የአውሮፓ ህብረት በስብሰባው ተወካያቸውን እንደሚልኩ ማረጋገጣቸውንም ነው ወልስትሪት ጆርናል የዘገበው።
ሳኡዲ ስብሰባውን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ከቻይና ጋር መልካም ግንኙነት ስላላት ነው የሚለው ዘገባው፥ የሞስኮ ወዳጅ ቤጂንግ በጂዳው ስብሰባ የመታደሟ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን ያብራራል።
በዚህ አለማቀፍ ምክክር ላይ ሩሲያ እንዳልተጋበዘች ተገልጿል።
ምዕራባውያን እና ዩክሬን በጋራ ባዘጋጁት ምክክር ላይ የሞስኮ አለመጋበዝ አይገርምም ያለው ሩሲያን ታይምስ (አርቲ)፥ ምክክሩ ዋነኛ አላማው እስካሁን ገለልተኛ አቋም የያዙ ታዳጊ ሀገራት ከኬቭ ጎን እንዲሰለፉ ጫና መፍጠር ስለመሆኑ ይገልጻል።
የጂዳው አለማቀፍ መድረክ በሰኔ ወር በዴንማርክ ኮፐንሃገን ከተካሄደው ምክክር እንደማይለይም በማከል።
በኮፐንሃገኑ ስብሰባ እንደ ህንድ እና ብራዚል ያሉ ሀገራት የፕሬዝዳንት ዜለንስኪን ባለ10 ነጥብ የሰላም እቅድ እንደማይፈርሙ መግለጻቸው ይታወሳል።
የሰላም እቅዱ የሩሲያን ከዩክሬን ግዛቶች መውጣት፣ የጦር ካሳ እና ሌሎች ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፥ ኬቭ በነዚህ ነጥቦች ላይ ሳንስማማ ከሞስኮ ጋር ለድርድር አልቀመጥም ብላለች።
ሩሲያ በበኩሏ የዜለንስኪ እቅድ የድርድር በሩን ለመዝጋት ያለመ ነው በሚል በተደጋጋሚ ተቃውማዋለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቅርቡ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ሲመክሩ ሞስኮ ለድርድር ክፍት ብትሆንም ምዕራባውያንና ኬቭ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አንስተዋል።
በምዕራባውያን ድጋፍ ለሁለት ቀናት በጂዳ የሚካሄደው ምክክርም ሀገራት ለዩክሬን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚጠየቅበት እንጂ ተፋላሚዎቹን ለማቀራረብ ያለመ አይመስልም።