የሩሲያ አየር ሃይል ወደ ቤልገሮድ የተተኩሶ ሶስት ሚሳኤሎችን መትቶ መጣሉን ገለጸ
ቤልጎሮድ በተባለው የዩክሬን አዋሳኝ አካባቢ የወደቁት ሚሳኤሎች በማን እንደተተኮሱ አልተጠቀሰም
ሚሳኤሎቹ በአንድ ሰውና በኤሌክትሪክ መሰረት ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ከመገለጹ ውጪ ዝርዝር መረጃን ሞስኮ ይፋ አላደረገችም
የሩሲያ አየር ሃይል ወደ ቤልገሮድ የተተኩሶ ሶስት ሚሳኤሎችን መትታ መጣሏን አስታወቀች።
ሚሳኤሎቹ በደቡባዊ ሩሲያ ቤልጎሮድ ሲወድቁ በጥቂቱ በአንድ ሰው ላይ የመቁሰል አደጋ ማስከተላቸው ተገልጿል።
ኖቪ ኦስኮል በተባለችው ከተማም የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት የቤልጎሮድ አስተዳዳሪው ቭላይቼስላቭ ግላድኮቭ።
አስተዳዳሪው የደረሰውን ጉዳት ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
“እስካሁን የደረሰን መረጃ አንድ ሰው እጁ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ብቻ ነው የሚያሳየው” ብለዋል ቭላይቼስላቭ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መረጃ።
ሩሲያን ከዩክሬኗ ክራኪቭ የሚያዋስነው ቤልጎሮድ ባለፈው አመት ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲያስተናግድ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
የዛሬውን የሚሳኤል ጥቃት ሙከራ ማን እንደፈጸመውም የቤልጎሮድ ግዛት አስተዳዳሪው ፍንጭ አልሰጡም።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ከዚህ ቀደም ለተፈጸሙ መሰል ጥቃቶች የዩክሬን መንግስትን ተጠያቂ ስታደርግ ቆይታለች።
ኬቭ በበኩሏ በሩሲያ ምድርም ሆነ በሞስኮ በተያዙ ግዛቶቿ ለተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶች አንድም ቀን ሃላፊነት ወስዳ አታውቅም።
ዩክሬን ባለፈው ወር ከአሜሪካ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን እንደምታገኝ መገለጹ የሚታወስ ነው።
2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ያወጣሉ የተባሉት ሚሳኤሎች ኬቭ ስለመድረሳቸውና ጥቅም ላይ መዋል ስለመጀመራቸው ግን አልተነገረም።