ሞስኮ በቀይ ባህር ፖለቲካ አለማቀፍ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ከአስመራ ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች ነው
ኤርትራ እና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 30ኛ አመት እያከበሩ ነው።
በፓስፊክ የምትንቀሳቀሰው “ማርሻል ሻፖሺኮቭ” የተሰኘች የሩሲያ መርከብም ምጽዋ መድረሷን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የኤርትራ ባህር ሃይልም ለሩሲያ አቻዎቹ ደማቅ አቀባበል ያደረገ ሲሆን፥ ትርኢቶችን ማሳየቱ ተገልጿል።
ሀገራቱ በቀጣይ አምስት ቀናትም ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ የተለያዩ መርሃግብሮችን እንደሚያካሂዱ ነው የተነገረው።
ከምዕራባውያን ጋር የተኳረፉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መስርተዋል።
ምዕራባውያኑ ፕሬዝዳንቱን “ለረጅም ጊዜ ምርጫ አላካሄዱም፤ ወጣቶችንም ወደ ትምህርት ቤት ሳይሆን ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ መላክን ይመርጣሉ፤ የሰብአዊ መብት አያያዛቸውም ሆነ ሀገራቸውን እየመሩበት ያለው መንገድ ከዴሞክራሲ ስርአት ጋር አይተዋወቅም” በሚል ደጋግመው ይወቅሷቸዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ግን ምዕራባውያኑ አደረግን የሚሉት ምርጫ የይስሙላ እና የሰብአዊ መብት አያያዛቸውም ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት እንደሆነ በራሳቸው መገናኛ ብዙሃኖች ሲሞግቷቸው ይደመጣሉ።
የምዕራባውያኑ የማዕቀብ ተጽዕኖ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ላይ የተቀመጠችውን ሀገር እድገት በብዙው እንደጎዳ ይታመናል።
ተጽዕኖውን ቀልብሶ ለመውጣትም እንደ ሩሲያ እና ቻይና ካሉ የአለም ስርአት በአንድ ሀገር የበላይነት ብቻ መመራት የለበትም ከሚሉ ሀገራት ጋር ጠንካራ የንግድና ወታደራዊ ትስስርን በመፍጠር ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው አመት በቤጂንግ በፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የተደረገላቸው አቀባበልም የዚህ ግንኙነት ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።
ፕሬዝዳንቱ የቻይና ቆይታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ሞስኮ በማቅናትም ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መምከራቸው አይዘነጋም።
አስመራ ከሞስኮ ጋር ያላት ግንኙነት ከቤጂንግ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነው።
ለዚህም ሶቪየት ህብረት በ1991 ከፈራረሰች በኋላ ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር አለመቻሏን በምክንያትነት ያነሳል ሁድሰን የተሰኘው የጥናት ተቋም።
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአፍሪካ ሀገራት ላይ አይኑን ጥሏል።
ሞስኮ ለአፍሪካውያን ሀገራት እዳ በመሰረዝ በየአመቱም በሴንትፒተርስበርግ የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤን ታሰናዳለች።
በአፍሪካ ቀንድ ግዙፍ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ባለው የቀይ ባህር ቀጠና ውስጥ የምትገኘው ኤርትራ ከሞስኮ ጋር የመሰረተችው ግንኙነት ከምዕራባውያን ያጣችውን የምታገኝበት ነው።
ሞስኮም ሃያላኑ በሚሻኮቱበት ቀጠና ለመግባትና አለማቀፍ ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ ከአስመራ ጋር መወዳጀቷ የሚኖረው ድርሻ ቀላል አይሆንም።
ኤርትራ የመንግስታቱ ድርጅት ሩሲያ በዩክሬን የከፈተችውን ጦርነት ለማውገዝ ባወጣቸው ሁለት የውሳኔ ሃሳቦች ላይ የተቃውሞ ድምጿን በማሰማት ከሞስኮ ጋር ለጀመረችው ግንኙነት የሰጠችውን ስፍራ አሳይታለች።