የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ጥቃት ሊያቆሙ የሚችሉት የእስራኤል ወረራ ከቆመ ብቻ ነው አሉ
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት እስራኤል በጋዛ እያደረገች ያለውን ወረራ ለመቃወም እና ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ይናገራሉ
የሀውቲ ታጣቂዎች ቃል አቀባይ "የእስራኤል ወረራ እና ከበባው እስከሚያበቃ ድረስ ፍልስጤማውያንን የሚረዳ ዘመቻ አይቆምም" ብሏል
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ጥቃት ሊያቆሙ የሚችሉት የእስራኤል ወረራ ከቆመ ብቻ ነው አሉ።
የሀውቲ ታጣቂዎች በትናንትናው እለት እንዳስታወቁት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታደርገውን ወረራ የምታቆም ከሆነ ብቻ በአለምአቀፉ የቀይ ባህር የንግድ መስመር ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ሊያቆሙ ይችላሉ።
የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስ ጥቃቱን ያቆሙ እንደሆነ የተጠየቀው የሀውቲ ቃል አቀባይ መሀመድ አቡዱልሰላም የጋዛ ከበባ ማብቃቱን እና የሰብአዊ እርዳታ ያለምንም እንቅፋት መድረሱን እንደሚገመግሙ ለሮይተርስ ተናግሯል።
ቃል አቀባዩ "የእስራኤል ወረራ እና ከበባው እስከሚያበቃ ድረስ ፍልስጤማውያንን የሚረዳ ዘመቻ አይቆምም" ብሏል።
ቃል አቀባዩ ይህን ያለው የሀውቲ ታጣቃዎች ጥቃት አድርሰዋል የሚል ሪፖርት ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ነው። ንብረትነቷ የግሪክ የሆነ እና የማርሻል ደሴቶችን ሰንደቅ አላማ እያውለበለበች ስትጓዝ ከነበረች መርከብ በሶስት ማይል ርቀት ላይ ሚሳይል ማረፉን የእንግሊዝ ሜማሪታይም ፈርም አምበርሊይ ገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) ማሪታይም ትሬድ ኦፐሬሽንም ችግሩ መከሰቱን አረጋግጦ፣ ሰራተኞቹ እና መርከቧ ሰላም መሆናቸውን እና ወደ ቀጣይ ወደብ ማቅናታቸውን ጠቅሷል።
የሀውቲ ታጣቂዎች ከባለፈው ህዳር ወር ወዲህ በቀይ ባህር እና በባብኤል ማንዴብ በኩል በሚልፉ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት አጠናክረው ቀጥለውበታል። ታጣቂዎቹ ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት እስራኤል በጋዛ እያደረገች ያለውን ወረራ ለመቃወም እና ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ይናገራሉ።
በጥቃቱ ምክንያት በርካታ አለምአቀፍ ኩባንያዎች የቀይ ባህር መስመርን እስከመቀየር ተገድደዋል።
ሀማስ በአደራዳሪዎች የቀረበለትን የ40 ቀናት የጋዛ ተኩስ አቀም ሰነድ ይዘት እያጠናው መሆኑን እንደሚገኝ ገልጿል።