ሩሲያ ወድ ዩክሬን መዲና 31 ሚሳኤሎችን ተኮሰች
ፑቲን ዩክሬን በቤልጎሮድ ለፈጸመችው ጥቃት ፈጣን አጻፋዊ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ በዛቱ ማግስት ነው የሚሳኤል ጥቃቱ የተፈጸመው
ኬቭ ሁሉንም ሚሳኤሎች መትታ መጣሏን ያስታወቀች ሲሆን፥ የሚሳኤሎቹ ስብርባሪዎች ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል
ሩሲያ ወደ ዩክሬኗ መዲና ኬቭ 31 ሚሳኤሎችን መተኮሷ ተነገረ።
ሞስኮ በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ ኬቭ ስትተኩስ ከ44 ቀናት በኋላ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
ሁሉም ሚሳኤሎች (2 ባለስቲክ እና 29 ክሩዝ ሚሳኤሎች) ተመተው ወድቀዋል ብሏል የዩክሬን አየር ሃይል።
ይሁን እንጂ የተመቱት ሚሳኤሎች ስብርባሪዎች ወደ መሬት ሲወድቁ በ13 ሰዎች ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ ተናግረዋል።
ኬቭ ከሌሎቹ የዩክሬን ከተሞች በብዙው የተሻለ የአየር መቃወሚያ ስርአት አላት።
የአሜሪካውን “ፓትሪዮት” የአየር መቃወሚያ የምትጠቀመው ከተማዋ ሚሳኤሎችን አየር ላይ መትቶ በመጣል ረገድ ጦርነቱ እንደተጀመረ ከነበረው አንጻር በእጅጉ የተሻለ አቅም እንደገነባች ነው አሶሼትድ ፕረስ የዘገበው።
ይሁን እንጂ የዩክሬን ባለስልጣናት አሁንም የምዕራባውያን ፈጣን ድጋፍ ካልተደረገልን ከባድ ጉዳት ይደርሳል በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በዛሬው የሚሳኤሎች ውርጅብኝ ከ80 በላይ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲወጡ ተደርጓል፤ የሚሳኤሎቹ ስብርባሪ በአንድ ህንጻ ላይ የእሳት አደጋ መፍጠሩና የቆሙ ተሽከርካሪዎችን ማውደሙን የዩክሬን የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ተቋም አስታውቋል።
ዩክሬን ባለፉት ቀናት በድንበር ከተማዋ ቤልጎሮድ የፈጸመቻቸው ተደጋጋሚ የሮኬት ጥቃቶች መፈጸሟ ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ ለፈጸመቻቸው ጥቃቶችም ፑቲን “ዋጋዋን ታገኛለች" ሲሉ መዛታቸው አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የዛሬውን አጻፋዊ መልስ መክበድ ተከትሎ ሞስኮ ከኬቭ ባሻገር በሌሎች ከተሞች የምትፈጽመውን የሚሳኤል ጥቃት አጠናክራ ልትቀጥል ስለምትችል ምዕራባውያን በፍጥነት ይድረሱልን የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ የአሜሪካ ሰራሹን “ፓትሪዮትስ” መቃወሚያ ጥሶ ጥቃት የሚያደርስ ሚሳኤል የላትም በሚል የሰጡት አስተያየትም ፑቲንን ፈገግ የሚያስብል ሳያስብል አይቀርም።