የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን ጨምሮ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት ውጤቱን ተቃውመው መግለጫ አውጥተዋል
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ዩክሬን እና ሉሎች ምእራባውያን ሀገራት አስተያየት ሰጥተዋል።
የሩሲያ ማእከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ሰብሳቢ እንዳስታወቁት፤ እስካሁን በተደረገ የድምጽ ቆጠራ ቭላድሚር ፑቲን 88 በመቶ ደምጽ በመግኘት በሰፊ ልዩነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም ፑቲንእስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ማለትም ለቀጣይ 6 ዓመታት በስልጣን ላይ የሚቆዩበትን እድል በድጋሚ አግኝተዋል ነው የተባለው።
ይህንን ተከትሎም ዩክሬን፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላድ እና ሌሎችም ሀገራት ውጤቱን ተችተው አስተያየት ከሰጡ ሀገራት መካከል ናቸው።
አሜሪካ
የአሜሪካ ዋይት ኃውስ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ምርጫው ነጻ እና ግልጽ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ፑቲን የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን በማሰር እና ሌሎቹንም ከምርጫው በማግለል ነው ያሸነፈው ብለዋል።
ዩክሬን
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በሰጡት መግለጫ፤ “የሩሲያው አምባገነን መሪ ቭላድሚር ፑቲን ሌላ የማስመሰል ምርጫ አድርጓል” ብለዋል። “ፑቲን ያደረገው ነገር የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ያደረገው እንደሆነ ዓለም ሁሉ ያውቀዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
“በዚህ የማስመሰል ምርጫ ምንም ህጋዊ ነገር የለም፤ ሊኖረውም አይችልም” ያሉት ዘለንስኪ፤ “ፑቲን መቅረብ ያለበት ዘ ሄግ በሚገኘው ችሎት ነው፤ ይህንንም ልናረጋግጥ ይገባል” ብለዋል።
ጀርመን
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤከስ ገጽ ባወጣው መግለጫ፤ “ሩሲያ ያካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻ ገለልተኛም አይደለም፤ ውጤቱም ማንንም አላስገረመም” ብሏል።
“የፑቲን አገዛዝ አምባገነናዊ ነው” ያለችው ጀርመን፤ አገዛዙ በሳንሱር፣ በጭቆና እና በአመጽ ላይ የተመሰረተ ነው” ስትልም ገልጻች።
ሩሲያ በያዘቻቸው ዩክሬን ግዛቶች ያደረገችው ምርጫም ባዶ እና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብሏል የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።
ብሪታኒያ
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በሩሲያ ምርጫ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “በሩሲያ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጠናቋል፤ በሩሲያ በተያዙ ዩክሬን አካባቢ ያሉ ሰዎችም ያለ ምንም አማራጭ ለመምረጥ ተገደዋል፤ ይህ ምኑም ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫን አይመስልም” ብለዋል።
ምእራባውያን እና ዩክሬን ምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊ አይደልም ብለው ቢያጣጥሉትም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ሩሲያ ያካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከየትኛውም የምእራባውያን ሀገራት የተሸለ እና በጣም ግልጸኝነት የታየበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።