ስጋቱን ተከትሎም ኢምባሲው ለአንድ ቀን ዝግ እንደሚሆንም አስታውቋል
በዩክሬን ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ በሩሲያ ጥቃት ምክንያት ተዘጋ፡፡
ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በተለይም አሜሪካ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ጦር መሳሪያ ሞስኮን እንድትመታ መፍቀዷን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል፡፡
ሁለቱም ሀገራት ከምድር ጦር ባለፈ የአየር ላይ ጥቃቶችን በስፋት እየተጠቀሙ ሲሆን በኪቭ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ ለአንድ ቀን እንደሚዘጋ አስታውቋል፡፡
ኢምባሲው ባወጣው ማስጠንቀቂያ መሰረት የኢምባሲው ሰራተኞች በያሉበት ሆነው ራሳቸውን ከአየር ላይ ጥቃቶች እንዲጠብቁም አሳስቧል፡፡
ሩሲያ በዛሬ ዕለት የአየር ላይ ጥቃት እንደምታደርስ መረጃ ደርሶኛል የሚለው ኢምባሲው አሜሪካዊያን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል ሲሰሙ ወደ ተሸለ ቦታ እንዲጠለሉ ብሏል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካንን ጨምሮ የብሪታንያ እና ፈረንሳይ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን ዩክሬን እንድትጠቀም መፍቀዳቸው ኔቶ በዚህ ጦርነት በቀጥታ እየተሳተፈ መሆኑን ማሳያ ነው ብላለች፡፡
ዩክሬንም የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅማ በሩሲያ ላይ ጥቃት የጀመረች ሲሆን ፕሬዝዳንት ፑቲን ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል፡፡
ፑቲን የሩሲያን የኒዩክሌር አጠቃቀም ህግ በማጽደቅ አሜሪካን አስጠነቀቁ
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪም ለዩክሬን ጥቃት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ህግንም እንደፈረሙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የስልጣን ዘመናቸውን ሊያጠናቅቁ ሁለት ወራት የቀራቸው የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለዩክሬን የረጅም ርቀት ጦር መሳሪያ መፍቀዳቸውን ተከትሎ በርካቶች ሶስተኛው ዓለም ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት አይሏል፡፡
የፕሬዝዳንት ባይደንን ውሳኔ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ በርካታ አሜሪካዊያን ፖለቲከኞች ተቃውመዋል፡፡