አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መላኳ በቀጥታ ለሩሲያ ስጋት መሆኑን ሞስኮ አስታውቃለች
ሩሲያ ከምዕራባዊያን ጋር ወታደራዊ ግጭት ልትጀምር እንደምትችል አስጠነቀቀች።
የሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሰባት ወራት ያለፉት ሲሆን ጦርነቱ በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
ለአብነትም ሩሲያ ባሳለፍነው ሳምንት አራት የዩክሬን ግዛቶችን በህዝበውሳኔ ወደ ሩሲያ የቀላቀለች ሲሆን፤ ዩክሬን በበኩሏ በተፋጠነ መንገድ የኔቶ አባል እንድትሆን ጥያቄ አቅርባለች።
የሩሲያ አዲስ ድርጊትን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት በሞስኮ ላይ አዲስ የማዕቀብ እቅዶችን ይፋ ያደረገ ሲሆን አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች።
በዋሸንግተን የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓ ለሩሲያ ቀጥታ የደህንነት ስጋትን ይደቅናል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ሩሲያ ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷ አይቀርም ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን በቀጠለ ቁጥር ጦርነቱ ከዩክሬን ውጪ የመዛመት እድል እንዳለው ስጋታቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ምዕራባዊያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን ከመስጠት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የቀጥታ ጦርነት እያደረገች ላለችው ዩክሬን አዲስ የጦር መሳሪያ የመስጠት እቅድ አላት የተባለ ሲሆን ለኪቭ ከሚሰጡት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ ሂማርስ የተሰኘው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ይገኝበታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የ625 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ከአሜሪካ ለዩክሬን ይሰጣል የተባለ ሲሆን አራት ላውንቸር፣ ጸረ ፈንጅ ሚሳኤል እና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በድጋፉ ውስጥ መካተታቸው ተገልጿል።