በዩክሬን ከተሞች ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ያለው የሩሲያው 'ግላይድ ቦምብ' ምንድነው?
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ እንዳሉት በመጋቢት ወር ብቻ 3000 የሚሆኑ እንዲህ አይነት ቦምቦች በሀገሪቱ ላይ ተጥለዋል
ሩሲያ በዚህ አመት በመጀመሪያ ላይ 1.5 ቶን ክብደት ያለው የተሻሻለ ግላይድ ቦምብ አስተዋውቃለች
ሩሲያ ግላይድ ቦምቦችን በመጠቀም በዩክሬን ከተሞች ከፍተኛ ውድመት እያደረሰች ትገኛለች።
ሩሲያ በዩክሬን በምታካሂደው የማጥቃት ዘመቻ ርካሽ ዋጋ ያላቸውን እና ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትሉትን ግላይድ ቦምቦችን በከፍተኛ መጠን እየተጠቀመች መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ሩሲያ በዚህ ሳምንት በካርካቭ አቅራቢያ ድንበር ጥሳ በገባችበት ወቅት የዩክሬኗን ሰሜናዊ ከተማ ቮቭቻንስክን ለመደብደብ 200 የግላይድ ቦምቦች ጥቅም ላይ ውለዋል ተብሎ ይታሰባል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ እንዳሉት በመጋቢት ወር ብቻ 3000 የሚሆኑ እንዲህ አይነት ቦምቦች በሀገሪቱ ላይ ተጥለዋል።
የቮቭቻንስክ ፖሊስ ኃላፊ ኦሌክሲ ካርኪቭስኪይ የግላይድ ቦምቦችን ጉዳት በቅርበት ማየት ችሏል።
"የግላይድ ቦምብ ያደረሰውን ጉዳት ለመግለጽ ቃላት የለኝም"ሲል የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ገልጿል።
ሩሲያ፣ በዩክሬን ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ገዳት እያደረሱ ያሉ ግላይድ ቦምቦችን መጠቀም የጀመረችው በቅርብ ወራት ነው። ግላይድ ቦምብ የሚሰራው በአርጌው የሶቬት ቦምብ ላይ አራት ክንፎች እና የአሰሳ ሳተላይት በመግጠም ነው። ዋጋቸው በጣም ቅናሽ ነው፤ ነገርግን ከፍተኛ ውድመት የማስከተል አቅም አላቸው።
የአውሮፓ የፖሊሲ ትንተና ማዕከል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ይህ ቦምብ በጠንካራ ምሽግ ታጥራ የነበረችው አብዲቪካ ባለፈው የካቲት ወር እንድትያዝ ወሳኝ ሚና ነበረው።
የሩሲያ ኃይሎች አሁን ላይ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬይን የምትገኘውን ካርኪቭን ለማጥቃት ጥቅም ላይ አውለውታል። ዩክሬን እስካሁን ጥቃቱን ለመቀልበስ እየሞከረች ትገኛለች።
የቮቭቻንስክ ፖሊስ ኃላፊ ሩሲያ እየገፋች ባለችበት የካርካቭ መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲወጡ እያደረጉ ናቸው።
"ባለፉት ስድስት ወራት በግላይድ ቦምብ ጥቃት ሲደርስብን ቆይቷል። ነገርግን በዚህ ወር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጨምሯል።"
ሩሲያ በቀላሉ የሚመረቱት ግላይድ ቦምቦች ከፍተኛ ክምችት አላት። ቦምቦቹ ፍሪፎል ወይም በቀጥታ የሚጣሉ ሳይሆኑ ከአውሮፕላን ላይ ረዘም ያለ ርቀት ተወንጭፈው በተገጠመላቸው ሳተላይት ኢላማዎችን በመለየት በትክክል መምታት የሚችሉ ናቸው።
ሩሲያ በዚህ አመት በመጀመሪያ ላይ የራሷን 1.5 ቶን ክብደት ያለው የተሻሻለ ግላይድ ቦምብ አስተዋውቃለች። ለግላይድ ቦምቦች የሚውለው ተተኳሽ ወይም ኦርዳንስ በአብዛኛው ኤፍኤቢ-1500 የተባለው ሲሆን ክብደቱም 1.5 ቶን ይሆናል።
የዩክሬን የደህንነት ተንታኝ የሆኑት ማሪያ ዞልኪና ለቢቢሲ እንደተናገሩት የግላይድ ቦምንድ ጥቅም ላይ መዋል የሚያስጨንቅ እና መሬት ላይ ያለው ወታራዊ ዘመቻ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያስገባ ነው።
የሩሲያ ኃይሎች እግረኛ ጦር ሳይጠቀሙ የዩክሬንን ምሽጎች እንዲሰብሩ አስችሏቸዋል ብለዋል ዞልኪና።