ሩሲያ በ10 ሀገራት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎችን እየገነባች ነው
ሞስኮ፥ ቻይና፣ ኢራን፣ ግብጽ እና ቱርክን ጨምሮ በ10 ሀገራት ነው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎችን እየገነባች የምትገኘው
የአለማቀፉ የአቶሚክ ሃይል ኤጀንሲ አለማችን በ2050 ከኒዩክሌር የምታገኘው ሃይል 950 ጊጋዋት እንደሚደርስ ተንብዩዋል
ሩሲያ በኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ግንባታ የአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ለመሆን እየሰራች መሆኑን አስታወቀች።
በክሬምሊን የዘላቂ ሃይል አለማቀፍ ትብብር ልዩ መልዕክተኛው ቦሪስ ቲቶቭ እንደገለጹት ሞስኮ በ10 ሀገራት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎችን እየገነባች ነው።
በቻይና፣ ግብጽ፣ ህንድ፣ ኢራን እና ቱርክን ጨምሮ በ10 ሀገራት እየተገነቡ የሚገኙት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎች ሩሲያን በዘርፉ ቀዳሚ እንደሚያደርጋትም ነው ያነሱት።
ሩሲያ በዩክሬን በጀመረችው ጦርነት ምክንያት የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ የወጪ ንግዷ ከፍተኛ ማዕቀብ ቢጣልበትም በኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎች ግንባታ ቀዳሚዋ ሆና ቀጥላለች።
በክሬምሊን የዘላቂ ሃይል አለማቀፍ ትብብር ልዩ መልዕክተኛው ቦሪስ ቲቶቭ፥ ሩሲያ ከዩራኒየም ሽያጭ ብቻ ሳይሆን በኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎች ግንባታ የአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር መሆን የሚያስችላትን ስራ እየከወነች ነው ብለዋል።
ሞስኮ በተለይም ከብክለት ነጻ የሆነ የሃይል አማራጭ የሚፈልጉ ታዳጊ ሀገራት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ገንቢልን ጥያቄ በብዛት እንደሚያቀርቡላት ትጠብቃለችም ነው ያሉት።
የሩሲያው ሩሳቶም ከኒዩክሌር ማብለያዎች ግንባታ እና ሌሎች አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ከ54 ሀገራት ጋር እንደሚሰራ የኖርዌይ የአለማቀፍ ጉዳዮች ተቋም ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ፋይናንሽያል ታይምስ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት በመላው አለም እየተገነቡ ከሚገኙ የኒዩክሌር ማብለያዎች ውስጥ ሲሶው በሩሲያ እንደሚከናወን መዘገቡ ይታወሳል።
በቡርኪናፋሶ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ጁንታ ባለፈው አመት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ለማስገንባት ከሩሲያ ጋር ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል። ኡዝቤኪስታን፣ ባንግላዲሽ እና ሀንጋሪም ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ የሩሲያን በኒዩክሌር ሃይል ከፊት የመሰለፍ ጥረት ለመግታት የሞስኮን የበለጸገ ዩራኒየም ላለማስገባት ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል።
ውሳኔው የሩሲያን ዩራኒየም በመግዛት ቀዳሚ የነበረችውን ዋሽንግተን በቤጂንግ ከመተካት ውጪ የተለየ ጫና እንዳልፈጠረባት አርቲ በቅርቡ ይዞት የወጣው ዘገባ ያመላክታል።
ሞስኮ ለኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ የሚውለውን ዩራኒየም በማብላላት አቅም አቅም ከአለማችን 44 በመቶውን ድርሻ የምትይዝ ሲሆን፥ ከበለጸገ ዩራኒየም ሽያጭ በየአመቱ ከ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ታገኛለች።
የአለማቀፉ የአቶሚክ ሃይል ኤጀንሲ በዚህ አመት ባወጣው ትንበያ አለማችን በ2050 ከኒዩክሌር የምታገኘው ሃይል አሁን ካለበት በ155 በመቶ አድጎ 950 ጊጋዋት ይደርሳል ማለቱ የሚታወስ ነው።