ሩሲያ በዩክሬን በኩል ለአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ መላክ አቆመች
የሩሲያው ጋዝፕሮም እና የዩክሬኑ ናፍቶጋዝ የተፈራረሙት የአምስት አመት ስምምነት በመጠናቀቁ ነው ሞስኮ በዩክሬን በኩል ነዳጅ መላክ ያቋረጠችው
በውሳኔው እንደ ስሎቫኪያ እና ሞልዶቫ ያሉ ሀገራት ክፉኛ ይጎዳሉ ተብሏል
ሩሲያ በዩክሬን በኩል ለአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ መላክ ማቆሟን አስታወቀች።
የሩሲያው ጋዝፕሮም እና የዩክሬኑ ናፍቶጋዝ የተፈራረሙት የአምስት አመት ስምምነት በመጠናቀቁ ነው ሞስኮ በዩክሬን በኩል ነዳጅ መላክ ያቋረጠችው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሩሲያ "በእኛ ደም ቢሊየኖችን እንድታገኝ አንፈቅድም" በማለት ስምምነቱ እንደማይታደስ መናገራቸው ይታወሳል።
ሩሲያ ከ1991 ጀምሮ በዩክሬን በኩል ለአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ ስትልክ የቆየች ሲሆን፥ ከየካቲት 2022 ወዲህ በዚህ መስመር የምትልከው ነዳጅ መጠን ቀንሷል።
ከዛሬ ጀምሮ በዩክሬን በኩል ነዳጇን ሙሉ በሙሉ መላክ ብታቆምም በጥቁር ባህር "ቱርክስትሪም" የነዳጅ ማስተላለፊያ በኩል ወደ ሀንጋሪ፣ ቱርክ እና ሰርቢያ መላክ ትችላለች።
የዩክሬኑ መስመር መዘጋት የአውሮፓ ሀገራት የሩሲያን ርካሽ ነዳጅ ማግኘታቸው እያበቃለት እንደሆነ አመላካች ነው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የአውሮፓ ህብረት ለአንድ አመት አማራጮችን ሲመለከትና ሲዘጋጅ መቆየቱን በመጥቀስ ውሳኔው የሚያስከትለው ጉዳት አነስተኛ ነው ቢልም እንደ ስሎቫኪያ ያሉ ሀገራት ክፉኛ እንደሚጎዱ ተገልጿል።
ሩሲያም ከፍተኛ ገቢ የሚያሳጣት ቢሆንም የበለጠ ዋጋ የሚከፍሉት የአውሮፓ ሀገራት መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስቀድመው ተናግረዋል።
የአውሮፓ ሀገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀች በኋላ ከሞስኮ የሚያስገቡትን የነዳጅ መጠን ቀንሰዋል። ምስራቃዊ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ግን አሁንም ድረስ የሩሲያ ነዳጅ ጥገኛ ናቸው። ሀገራቱ ከሩሲያ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ነዳጅ በየአመቱ ያስገባሉ።
የአውሮፓ ሀገራት በ2021 ካስገቡት ነዳጅ የሩሲያ ድርሻ 40 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2023 ወደ 10 በመቶ ዝቅ ብሏል።
እንደ ስሎቫኪያ እና ኦስትሪያ ያሉ ሀገራት ግን ከሩሲያ ከፍተኛ ነዳጅ ማስገባታቸውን ቀጥለዋል።
የሩሲያ ነዳጅ ወደ ኦስትሪያ፣ ሀንጋሪ እና ጣሊያን ሲላክ የትራንዚት እና መግፊያ ገንዘብ የምታገኘው ስሎቫኪያ የሩሲያ ነዳጅ በዩክሬን በኩል መተላለፍ መቋረጡን ተቃውማለች።
ባለፈው አርብ በሞስኮ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የመከሩት የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ ለዩክሬን ኤሌክትሪክ መላክ ልናቋርጥ እንችላለን ሲሉ ዝተዋል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆነችው ሞልዶቫ የሩሲያ እና ዩክሬን የነዳጅ ማስተላለፍ ስምምነት መጠናቀቅ ከሚጎዳቸው ቀዳሚ ሀገራት ውስጥ ተመድባለች። አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫዎቿ በሩሲያ ነዳጅ የሚንቀሳቀሱት ሞልዶቫ ዜጎቿ ሀይል እንዲቆጥቡ ጥሪ አቅርባለች።