የአውሮፓ ህብረት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጡ በሚል ሲዘጋጅ መቆየቱ ይታወሳል
ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ ሀገራት የአሜሪካን ነዳጅ እንዲገዙ አስጠነቀቁ፡፡
ከአንድ ወር በኋላ በይፋ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት የሚገቡት ዶናልድ ትራምፕ ከወዲሁ የአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲያቸውን ተግብረዋል፡፡
ቻይናን ጨምሮ ሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ ግብር እንደሚጨምሩ የጠናገሩት ትራምፕ አሁን ደግሞ የአውሮፓ ህብረትን አስጠንቅቀዋል፡፡
ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሉት “የአውሮፓ ህብረት የአሜሪካንን ነዳጅ በገፍ እንዲገዙ ነግሬያቸዋለሁ፣ ይህ ካልሆነ ግን ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶቻቸው ላይ የታሪፍ ጭማሪ ይጠብቃቸዋል” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት ዋነኛ የነዳጅ አቅራቢ የነበረችው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ የገበያ ድርሻዋ ቀንሷል፡፡
ከሩሲያ ጥገኝነት መላቀቅ አለብኝ ያለው የአውሮፓ ህብረት ላለፉት ሶስት ዓመታት ከአሜሪካ እና ኖርዌይ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ሲገዛ ቆይቷል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በተደረገ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድል የቀናቸው ዶናልድ ትራምፕ አውሮፓ ተጨማሪ ነዳጅ ከአሜሪካ እንዲገዛ ጫና ማድረግ ጀምረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ የዶናልድ ትራምፕን አስተያየት እንዳየው ገልጾ በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ከአሜሪካ ጋር ጥሩ የንግድ ግንኙነት እንደለው አሳውቋል፡፡
በአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲያቸው የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ ከሜክሲኮ እና ካናዳ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የግብር ጭማሪ እንደሚያደርጉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ ካናዳ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ አደርጋለሁ ካሉ በኋላ በሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት የተከሰተ ሲሆን ኦታዋ የተባለችውን ካላደረገች የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት ሆና ትቀላቀለን ብለዋል፡፡