ሩሲያ ጦሯን በህዝበ ውሳኔ ወደ ራሷ ከጠቀለለቻት ኬርሰን ግዛት አስወጣች
ከ100 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ እንደሆነ የአሜሪካ ጦር መሪ ተናግረዋል
ዩክሬን በበኩሏ የሩሲያ ጦር ከኬርሰን ሙሉ ለሙሉ መውጣቱን እንደማታምን ገልጻለች
ሩሲያ ጦሯን በህዝበ ውሳኔ ወደ ራሷ ከጠቀለለቻት ኬርሰን ግዛት አስወጣች፡፡
ሩሲያ ከስምንት ወር በፊት ለጥቂት ቀናት ለተዘጋጀ ልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን የላከችው ጦር እስካሁን ወደ ሀገሩ አልተመለሰም፡፡
ከሁለት ወር በፊት አራት የዩክሬን ግዘቶችን በህዝበ ውሳኔ ወደ ራሷ የጠቀለለችው ሩሲያ ኬርሰን ፣ዶምባስ፣ ሉሃንስ እና ዛፖራዚየ ግዘቶች ደግሞ ህዝበ ውሳኔው የተካሄደባቸው የዩክሬን ግዛቶች ናቸው፡፡
የሩሲያ ጦር ከነዚህ አራት ግዛቶች መካከልም ኬርሰን ተብሎ ከሚጠራው ግዛት ለቆ መውጣቱን ሞስኮ ያስታወቀች ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በዩክሬን ጦር ላለመቆረጥ እንደሆነ የሐገሪቱ ወታደራዊ መሪዎች ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጊ ሼጉ እንዳሉት በኬርሰን እና አካባ ቢው ያለው ጦራቸው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ መታዘዙን ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ በኬርሰን እና አካባቢው የሰፈረው የሩሲያ ጦር በተወሰነ መልኩ ይልቀቅ እንጂ ጦሩ አካባቢውን ለቆ አለመሄዱን እና የሩሲያን ጦር ከደቡባዊ ዩክሬን ግዛቶች ለማስለቀቅ ጥቃቴን እቀጥላለሁ ብላለች፡፡
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የደህንነት አማካሪው ኦሌክሲ አርስቶቪች እንዳሉት የሩሲያ ጦር ሙሉ ለሙሉ አለመልቀቁን ገልጸው ተጨማሪ እና ድጋፍ የሚያደርግ ጦር መልሶ ወደ ኬርሰን ሊገባ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ እንዳሉት የሩሲያ ጦር ኬርሰንን ለመልቀቅ መገደዱን ተናግረው ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ100 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኬርሰን ግዛት በሩሲያ ጦር ከተያዙት ግዛቶች መካከል የክልል ከተማ ስትሆን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኬቭ የሚፈሰው ድኒፕሮ ወንዝ መነሻ እና በፈረንጆቹ 2014 ላይ በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ለተካለለችው ክሪሚያ ግዛት ጋር የፈጣን መንገድ ያላት ቁልፍ ከተማ እንደሆነች ተገልጿል፡፡
ዩክሬን ወታደሮችም ዋነኛ የመልሶ ማጥቃት ማዕከል የሖነችው ኬርሰን ግዛት የሩሲያ ጦር ለቆ ቢወጣም ዩክሬን በቀላሉ መልሳ ላትይዛት ትችላለችም ተብሏል፡፡
ሩሲያ የኬርሰን ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎችን አስቀድማ ያሸሸች ሲሆን በአካባቢው ባለው የዩክሬን ወታደሮች ላይ አዲስ ጥቃት ልትከፍት እንደምትችል ይጠበቃል፡፡