ሩሲያ ወታደሮቿ በአቭዲቪካ እና በዶኔስክ ዙሪያ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች መያዛቸውን ገለጸች
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዚህ ሳምንት ሁለት አመት አልፎታል
ዩክሬን በአንጻሩ ከአቭዲቪኻ ጦሯን ያስወጣችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍ በተፈለገው ጊዜ ባለመድረሱ መሆኑን ገልጻለች
ሩሲያ በዛሬው እለት እንዳስታወቀች ወታደሮቿ በአቭዲቪካ እና በዶኔስክ ጠቃሚ ወታደራዊ ቦታዎችን መያዛቸውን አስታወቃለች።
ወታደሮቹ የተሻለ ቦታ የያዙት አቭዲቪካን የተቆጣጠሩት ወታደሮች ወደፊት እንዲገፉ ፕሬዝደንት ፑቲን ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው የሩሲያ ኃይሎች በዶኔስክ ክልል ውስጥ ከአቭዲቪካ በቅርብ ርቀት በሚገኙት በክሊሽቺቭካ፣ ዲለይቪካ እና ኩርዲሚቪካ ቦታዎች ላይ ጠቃሚ የሆኑ ቦታዎችን ይዘዋል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው የሩሲያ ጦር በእነዚህ ሶስት ቦታዎች የሚገኙትን የዩክሬን 22ኛ፣28ኛ እና 92ኛ ብርጌዶችን አሸንፏል።
ሚኒስቴሩ በአቭዲቪካ በኩል ያለውን የዩክሬን ጦርም ከቦታው ማስለቀቅ መቻሉን ጠቅሷል። እንደሚንስቴሩ ከሆነ 77 የዩክሬን ድሮኖች ተመትተው ወድመዋል።
አቭዲቪካ ከተያዘች በኋላ ፕሬዝደንት ፑቲን የተገኙ ድሎችን ለማጠናከር ወደ ዩክሬን ይዞታዎች ማጥቃታቸውን እንደሚገፉ ባለፈው ማክሰኞ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአቭዲቪካ መያዝ ሩሲያ ባለፈው ሰኔ ወር ባክመትን ከያዘች በኋላ ያገኘችው ትልቅ ድል ነው ተብሏል።
ዩክሬን በአንጻሩ ከአቭዲቪኻ ጦሯን ያስወጣችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍ በተፈለገው ጊዜ ባለመድረሱ መሆኑን ገልጻለች።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዚህ ሳምንት ሁለት አመት አልፎታል።