ሩሲያ እስከ ኬቭ መዝለቋ አይቀርም - ሜድቬዴቭ
የሩሲያ የደህንነት ምክርቤት ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የኦዴሳ ወደብንም በቁጥጥር ስር እናውላለን ብለዋል
ሩሲያ ከነገ በስቲያ ሁለተኛ አመቱን በሚደፈነው ጦርነት ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬን መሬት ይዛለች
ሩሲያ ከሁለት አመት በፊት በዩክሬን የጀመረችው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ መቋጫው ኬቭና ኦዴሳ እንደሚሆን የቀድሞው የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ተናገሩ።
አቪድቭካ ከተማን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው የሩሲያ ጦር የድል ግስጋሴው ይቀጥላል ነው ያሉት የሩሲያ የደህንነት ምክርቤት ሊቀመንበሩ ሜድቬዴቭ።
“ጦርነቱ የት ይቁም? አላውቅም፤ አሁን ባለበት እንደማይቆም ግን እርግጠኛ ነኝ” ሲሉም ተደምጠዋል።
የዩክሬን ወታደሮች የሩሲያን ምት መቋቋም ተስኗቸው እየተበታተኑ መሆኑንም ሜድቬዴቭ ከሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል።
ሩሲያ በየካቲት 2022 ወደ ዩክሬን በዘለቀች ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ መዲናዋ ኬቭ ብትቃረብም ከተማዋን በቁጥጥር ስር ማዋል አልቻለችም።
ሞስኮ ወደ ኬቭ በየቀኑ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃቶችን በመፈጸም ከባድ ጉዳት ማድረሷ ይታወቃል።
የሜድቬዴቭ አስተያየትም ሩሲያ በአውደ ውጊያ ያላትን የበላይነት የሚያሳይና የሞስኮን መተማመን ያሳያል ተብሏል።
ከምዕራባውያን በቂ ድጋፍ አልደረሰኝም የምትለው ዩክሬን በሰኔ ወር የጀመረችውን የመልሶ ማጥቃት ማስቀጠል አልቻለችም።
ከነገ በስቲያ ሁለት አመት በሚደፍነው ጦርነት ሩሲያ ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬን መሬት ይዛለች።
ሞስኮ በጦሯ የተያዙ አካባቢዎች ከእንግዲህ የሩሲያ አካል መሆናቸውን ያስታወቀች ሲሆን፥ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን መሬታችን ካላስመለስን እንቅልፍ አይወስደኝም ማለታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ምዕራባውያን ባለፉት ሁለት አመታት ለዩክሬን ከ270 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ቢያደርጉም ሩሲያን ከዩክሬን ማስወጣት አልተቻላቸውም።