13 የሩሲያ ድሮኖች በዩክሬን የአየር መቃወሚያ ተመተው መውደቃቸውም ተገልጿል
ሩሲያ በኢራን ሰራሽ ድሮኖች በዩክሬን መዲና ኬቭ ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ።
የኬቭ ከተማ ከንቲባ ቪታል ክሊትሽኮ እንዳስታወቁት፥ በድሮን ጥቃቱ ሁለት የአሰተዳደር ህንጻዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከንቲባው በሰው ህይወት ላይ ስለደረስ ጉዳት ግን የተናገሩት ነገር የለም።
ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ የሚኖሩ ዩክሬናውያን ጉዳት እንዳይደርስባቸው በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተገልጿል።
የዩክሬን አየር ሃይል ቃል አቀባይ ዩሪ ኢህናት ፥ ጥቃቱ ንጹሃን በተኙበትና ድሮኖች ከእይታ በሚሰወሩበት ሌሊት ላይ መፈጸሙን ተናግረዋል።
የዩክሬን የአየር መቃወሚያዎች ግን 13 ድሮኖችን መትቶ በመጣል ውጤታማ ስራን ሰርቷል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
በዛሬው ጥቃት ምን ያህል ድሮኖች መሳተፋቸው እየተጣራ መሆኑንም አንስተዋል።
ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክትም በአየር ሃይላቸው እርምጃ ኩራት እንደተሰማቸው ነው የገለጹት።
ሩሲያ በበኩሏ ከዩክሬን በኩል ስለቀረበው ክስም ሆነ ድሮኖቿ ተመተው ስለመውደቃቸው ያለችው ነገር የለም።
ሞስኮ ከቴህራን ያገኘቻቸው ድሮኖችን በዩክሬን ጦርነት የመጠቀሟ ጉዳይም አሁንም የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቀጥሏል።