የጸረ-አየር ሚሳይል ሙከራው የተፈለገውን "ዒላማ" ትክክለኛነት የመምታት ተግባር መፈጸሙ ተነግሯል።
ሩሲያ አዲስ የአየር መከላከያ ስርዓትን አስተዋወቀች
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር እንዳስታወቀው የሀገሪቱ ኤሮስፔስ ኃይሎች በሳሪ ሻጋን ካዛኪስታን በተደረገ የጸረ-አየር ሚሳይል ሙከራ ለአየር መከላከያ ስርዓት የሚሆን መሳሪያን በተሳካ ሁኔታ ሞክረዋል።
የሩሲያ የዜና ወኪል ስፑትኒክ የመከላከያ ሚንስቴርን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በሳሪ-ሻጋን ሜዳ ላይ ከሩሲያ አየር እና የሚሳይል መከላከያ ሰራዊት የተውጣጣው ተዋጊ ቡድን አዲስ የሙከራ ጅምር አካሂዶ ተሳክቶለታል።
ሙከራው ለሩሲያ አዲስ የሚሳይል መከላከያ ስርዓትን ያስተዋወቀ ነው ተብሏል።
የሩስያ ኤሮስፔስ ኃይል የሚሳኤል መከላከያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሰርጌይ ግራብቹክ አዲሱ ሚሳይል ከተከታታይ ሙከራዎች በኋላ ማሟላት ያለበትን ዝርዝር አረጋግጧል ብለዋል። ሙከራውን የከወኑት ተዋጊዎቹም የተፈለገውን "ዒላማ" ትክክለኛነት የመምታት ተግባር መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር ሩሲያ የኒውክሌር ጦር ጭንቅላትን መሸከም የሚችለውን "ሳርማት" የተባለ አህጉር አቀፍ ሚሳይል በተሳካ ሁኔታ ሙከራ ማድረጓ ታውቋል።
የሳርማት ሚሳኤል 18 ሽህ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው እና የኒውክሌር ጦርን የሚይዝ ሲሆን፤ ይህም ሩሲያ በሰሜን ወይም በደቡብ ዋልታዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር በዓለም ዙሪያ ኢላማዎችን እንድትደርስ ያስችላታል ተብሏል።
እነዚህ የሚሳይል ሙከራዎች የተከሰቱት ሩሲያ ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻን ስትፈጽም በነበረችበትና ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን ተቃውሞ በገጠማት ወቅት እንደሆነም ተነግሯል።
ሞስኮ በዚህ እንቅስቃሴዋም የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲጣልባት ምክንያት ሆኗል።