አውሮፓውያን በሞስኮ ላይ ማዕቀብ ቢጥሉም ዋነኛ የሩሲያ ጋዝ ሸማቾች መሆናቸው ተገለጸ
ሀገራቱ ከዩክሬን ጦርነት በፊት ይገዙት ከነበረው መጠን በ40 በመቶ ጨምሯል ተብሏል
ስፔን፣ ቤልጂየም እና ፈረንሳይ ቀዳሚዎቹ የሩሲያ ጋዝ ሸማች ሀገራት ናቸው
አውሮፓውያን በሞስኮ ላይ ማዕቀብ ቢጥሉም ዋነኛ የሩሲያ ጋዝ ሸማቾች መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ሩሲያ ጦሯን ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ በአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ከ12 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል፡፡
ማዕቀቡ በዋናነት የሩሲያን ኢኮኖሚ ለመጉዳት ተብለው የተጣሉ ሲሆን ሞስኮ በዓለም የምትታወቅበት የነዳጅ ንግዷን ለመጉዳት በሚል የዋጋ ተመን ከመጣል ጀምሮ በርካታ ማዕቀቦች ተጥለዋል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ ዋነኛ ማዕቀብ ጣይ ሀገር ቢሆኑም ከየትኛውም ሀገር በላይ የሩሲያን ጋዝ ሸምተዋል ሲል ግሎባል ዊትነስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ አውሮፓዊያን በያዝነው ዓመት ከጥር እስከ ሀምሌ ባሉት ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ 21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነዳጅ ከሩሲያ ገዝተዋል፡፡
የተገዛው የነዳጅ መጠን የዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
ስፔን፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ ፣ ቱርክ፣ ኔዘርላንድ እና ግሪክ ደግሞ የሩሲያን ጋዝ በመግዛት ከቻይና በመቀጠል ቀዳሚ ሀገራት እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ኖርዎይ ወደ ሩሲያ ይሄዳሉ በሚል ስጋት በርካታ አጋዘኖችን አረደች
ሩሲያ ለዓለም ከሸጠችው የተጣራ ነዳጅ ውስጥ 52 በመቶውን የገዙት አውሮፓዊያን እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ ሩሲያ ከአውሮፓ ሀገራት ከአምስት ቢሊዮን በላይ ዩሮ ከነዳጅ ሽያጭ ገቢ አግኝታለች ተብሏል፡፡
አሜሪካ ለአውሮፓ ሀገራት ቀዳሚዋ ነዳጅ አቅራቢ ሀገር ስትሆን ሩሲያ፣ ኳታር፣ አልጀሪያ፣ ኖርዌይ እና ናይጀሪያ ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ የዓለማችን ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች የሩሲያን ነዳጅ እየገዙ በሌላ ሀገር ስም እየሸጡ ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ቃል አቀባይ በበኩሉ ህብረቱ ከሩሲያ የነዳጅ ጥገኝነት በመላቀቅ ላይ መሆኑን ገልጾ ዘገባውን ውድቅ አድርጓል፡፡