የኔቶ ልዩ ጦር ወደ ዩክሬን ምድር መግባቱ ተገልጿል
ሩሲያ ከኔቶ ጦር ጋር ለመዋጋት በቂ ምክንያት እንዳላት ተገለጸ፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 450 ቀናት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ እንዲቆም የተለያዩ ጥረቶች በበርካታ ሀገራት ቢደረጉም እስካሁን መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ የኔቶ አባል ሀገራት እና ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ ሀገራት ለዩክሬን የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ ያሳሰበች ቢሆንም ለኪቭ የሚሰጠው ድጋፍ እንደቀጠለ ነው፡፡
ዩክሬንም በድጋፍ መልክ ባገኘቻቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ወደ ሩሲያ ምድር ዘልቃ በመግባት ተደጋገሚ ጥቃቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ይህንን ተከትሎም የሩሲያ ጸጥታ ምክር ቤት ሃለፊ የሆኑት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ሩሲያ ከኔቶ ጋር የቀጥታ ጦርነት የመጀመር መብት አላት ብለዋል፡፡
ዩክሬን በሩሲያ ላይ ለምትሰነዝራቸው እያንዳንዱ ጥቃቶች የኔቶ ድጋፍ እና ይሁንታ አለው ያሉት ሜድቬዴቭ ይህም ሩሲያ ከኔቶ ጋር ጦርነት ለመጀመር በቂ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሩሲያ አዲስ የአየር ሀይል ወታደራዊ አዛዥ ሾመች
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ የኔቶ ልዩ ወታደሮች በዩክሬን ግዛት ውስጥ የገቡ ሲሆን ወታደሮቹ ለምን ዓላማ እንደገቡ እስካሁን አልተገለጸም፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በጊዜ ካልተቋጨ ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት መጀመር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡
ሩሲያ ብሔራዊ ሉዓላዊነቴ ጥያቄ ውስጥ ከገባ የኑክሌር አረር ጦር መሳሪያዬን ለመጠቀም እገደዳለሁ በሚል ማስጠንቀቋ አይዘነጋም፡፡
ሞስኮ በተደጋጋሚ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልምምድ በየብስ፣ ባህር እና ሀይር ሀይሏ አማካኝነት ያካሄደች ሲሆን የተወሰኑ መሳሪያዎችን ወደ ጎረቤት ሀገር ቤላሩስ እንዲሰፍርም አድርጋለች፡፡