ዩክሬን በአንድ ቀን ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮችን መግደሏን አስታወቀች
በሳለፍነው ግንቦት ወር 35ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ሩሲያ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል
ሁለቱ ተፋላሚዎች እርስ በእርስ የሚያወጧቸውን የተጋነኑ የጉዳት መጠኖች በገለልተኛ አካል ማጣራት አልተቻለም
ዩክሬን በአንድ ቀን ውስጥ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ አስር በላይ የሩሲያ ወታደሮችን መግደሏን አስታወቀች፡፡
በትላንትናው እለት ሞተዋል ተብሎ ይፋ ከተደረገው የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር ባለፈ 115 ከፍተኛ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ፣ 19 ታንኮች እና 66 መድፎችን ማውደሟን ኪቭ አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ ከቀናት በፊት በዶኔስክ ክልል የሚገኙ ሁለት ተጨማሪ ስትራቴጂካዊ ስፍራዎችን መቆጣጠሯን ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት 2022 ጀምሮ ከ543ሺ በላይ የሩሲያ ወታደሮች መሞት እና መቁሰላቸውን የገለጸው የዩክሬን መከላከያ ሚንስቴር በአጠቃላይ ከ14ሺ በላይ የሞስኮ መድፎች መውደማቸውን አስታውቋል፡፡
መግለጫው አክሎም ሩስያ በየወሩ 30ሺ አዳዲስ ምልምሎችን ወደ ጦሩ እንደምታቀላቅል ነው ይፋ ያደረገው፡፡
ሀገራቱ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ በየግላቸው የሚያወጡትን የጉዳት መጠን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም ባሰለፍነው ግንቦት ወር የብሪታንያ መከላከያ ሚንስቴር ይፋ ባደረገው ሪፖርት በጦርነቱ ሩስያ በ500 ሺህ ወታደሮቿ ላይ የሞት እና መቁሰል ጉዳት ማስመዝገቧን ገልጿል፡፡
በየቀኑ ከ1200 በላይ የሩሲያ ወታደሮች ህይወታቸውን እንደሚያጡ የገለጸው የብሪታንያ መከላከያ ሪፖርት በዩክሬን በኩል የደረሰውን ጉዳት አላካተተም፡፡
የሩሲያ የመከላከያ ሚንስቴር በበኩሉ በግንቦት ወር ብቻ 35ሺ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ሚንስቴሩ ከሞቱት ወታደሮች በተጨማሪ በወሩ ዩክሬን ቁጥራቸው 2700 የሚሻገር ከባባድ የጦር መሳርያዎች ወድመውባታል ነው ያለው፡፡
290 ታንኮች እና ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች እንደወደሙ ከነዚህ መካከል 4 አሜሪካ ሰራሹ አብራም ታንክ፣ 7 የጀርመኑ ሊዮፓርድ ታንኮች እንዲሁም 11 አውሮፕላኖች፣ 4 ሄሊኮፕተሮች እና የሮኬት ማስወንጨፊያ መሳርያዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የሞተብኝ ጦር 31 ሺህ ብቻ ነው ትላለች። የአሜሪካ ባለስልጣናት ደግሞ በጦርነቱ 70ሺ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
በንጹሀን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በተመለከተ በ2024 መጀመርያ ወር ላይ ሪፖርት ያወጣው ኦክስፋም አሜሪካ የተሰኝው ግብረ ሰናይ ድርጅት፤ በጦርነቱ በአማካይ 42 ንጹሀን ሰዎች በቀን ህይወታቸው እንደሚያልፍ የገለጸ ሲሆን አጠቃላይ የንጹሀን ሟቾች ቁጥር ደግሞ 10ሺህ 500 ነው ብሏል፡፡