ሩሲያ ዚርኮን የተባለውን ሀይፐርሶኒክ ሚሳይል በዩክሬን ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀሟ ተገለጸ
ሩሲያ ከዚህ ቀደም እንደገለጸችው ከሆነ ዚርኮን ሚሳይል 1000 ኪሎሜትር የሚምዘገዘግ እና ከድምጽ በዘጠኝ እጥፍ የሚፈጥን ነው
ሩሲያ በዩክሬን በምታደርገው ጦርነት ዚርኮን ሀይፐርሶኒክ የተባለውን ሚሳይል ጥቅም ላይ ማዋሏን ተመራማሪዎች ገልጸዋል
ሩሲያ በዩክሬን በምታደርገው ጦርነት ዚርኮን ሀይፐርሶኒክ የተባለውን ሚሳይል ጥቅም ላይ ማዋሏን ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
የኪቭ ጥናት ተቋም በትናንትናው እለት እንደገለጸው ያደረገው የቅድመ ጥናት ትንተና ሩሲያ ሁለት አመታትን ባስቆጠረው ጦርነት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ዚርኮንን በመጠቀም ኪቭን መምታቷን ያሳያል።
በኪቭ ሳይንሳዊ ጥናት ተቋም የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክተር የሆኑት ኦሌክሳንደር ሩቪን በቴሌግራም ገጻቸው ሩሲያ የካቲት ሰባት ካስወነጨፈችው ሚሳይል ላይ በተገኙ ስብርባሪዎች ላይ የተካሄደው የመጀመሪያው ትንተና መጠናቀቁን ገልጿል።
ኃላፊው የዚርኮን ሚሳይል ስብርባሪዎችን ያሳያል ያሉትን ቪዲዮም ለቀዋል።
ሮይተርስ በጉዳዩ ዙሪያ ከሩሲያ በኩል ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም እንደገለጸችው ከሆነ ዚርኮን ሚሳይል 1000 ኪሎሜትር የሚምዘገዘግ እና ከድምጽ በዘጠኝ እጥፍ የሚፈጥን ነው።
የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኞች የሚሳይሉ ፍጥነት የአየር መከላከያ ምላሽ ለመስጠት የሚወስድበትን ጊዜ በእጅጉ የሚቀንስ እንደሚሆን ይናገራሉ።
ሩሲያ ቀደም ሲል የዚርኮን ሚሳይል ሙከራን በ2022 ማጠናቀቋን ገልጻ ነበር። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ዚርኮንን ተወዳዳሪ የሌለው የአዲስ ትውልድ ሚሳይል ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሩሲያ ይህን ሚሳይል በዩክሬን መጠቀሟ ከተረጋገጠ፣ ከምዕራባውያን ወታደራዊ እርዳታ ማግኘቷ ጥያቄ ውስጥ ለወደቀባት ዩክሬን አየር መከላከያ ስርአት ተጨማሪ ፈተና ይሆናል ተብሏል።
ሩሲያ የተለያየ ርቀት የሚጓዙ ሚሳይሎችን በመጠቀም በዩክሬን ላይ ጥቃት እያደረሰች ትገኛለች።