ሩሲያ ለዩክሬኑ ጦርነት አዲስ ጀነራል ሾመች
ሞስኮ በአራት ወራት ውስጥ ጀነራል መቀየሯ 11ኛ ወሩን የያዘው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ እንደማይቀር ያሳያል ተብሏል
በሌላ በኩል የሩስያው የግል ምልምል ወታደሮችን አቅራቢያ ዋግነር በዩክሬን ሶሌዳር የተሰኘችውን ከተማ መቆጣጠሩን አስታውቋል
ሩሲያ በዩክሬኑ ምድር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የሚመራ አዲስ ወታደራዊ አዛዥ መሾሟን ይፋ አድርጋለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ እንዳስታወቁት፥ ቫለሪ ገራሲሞቭ ሞስኮ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” የምትለውን ጦርነት እንዲመሩ ተሹመዋል።
ገራሲሞቭ ከአራት ወራት በፊት ተሹመው የነበሩትን ጀነራል ሰርጌ ሱሮቪኪን ተክተው አጠቃላይ ጦርነቱን ይመራኩ ተብሏል።
አዲሱ ሹመትም 11ኛ ወሩን የያዘው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን ያመላክታል ተብሏል።
በጦርነቱ ድል ከራቃት ስድስት ወራት ያለፋት ሞስኮ በ2023 በየትኛውም መስዋዕትነት ድል ለመቀዳጀት በፕሬዝዳንቷ በኩል ለዜጎቿ የዘመቻ ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል።
በሌላ በኩል የሩስያው የግል ምልምል ወታደሮችን አቅራቢያ ዋግነር በዩክሬን ሶሌዳር የተሰኘችውን ከተማ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን አስታውቋል።
የፕሬዝዳንት ፑቲን የቅርብ ሰው ናቸው የሚባልላቸው የዋግነር መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዚን፥ የጨው ማምረቻዋን ከተማ ለመቆጣጠር በተካሄደው ውጊያ ከ500 በላይ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ከጦርነቱ በፊት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚኖሩባት ከተማ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ስለመዋሏ ዋግነር ትናንት ለሰጠው አስተያየት ከዩክሬን በኩል ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልተሰጠም።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን ከዚህ ቀደም ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ከተማዋ ለይ ውጊያ ቢኖርም በሩስያ ሃይሎች አለመያዟን መናገራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሊውድ ኦስቲንም ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ ሶሌዳር በሩስያ ስር ስለመግባቷ እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልም ሲሉ ተደምጠዋል።
ዋግነር በቁጥጥር ስር እንዳዋላት የተናገረላት የሶሌዳር ከተማ የዩክሬን ምስራቃዊ የኢንዱስትሪ ከተሞችን ለመያዝ ስትራቴጂካዊ ፋይዳዋ የላቀ ነው ተብሏል።
ክሬምሊን ግን ከተማዋ ስለመያዟም ሆነ ስለደረሰው ጉዳት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።