ምዕራባውያን "አስፈሪው ወታደራዊ አውሬ" ብለው የሚጠሩት የሩሲያ የጦር መሳሪያ
ታዋቂው የሩሲያ ጦር መሣሪያ አስደናቂ ወታደራዊ ትጥቅ እንዳለው ይነገርለታል
“Tu-160 M2” ግዙፉ የጦር አውሮፕላን በሰዓት እስከ 2 ሺህ ኪ.ሜ መብረርና እስከ 40 ቶን የሚመዝን ቦምብ መጣል ይችላል
4 ሺህ 145 የጦር አውሮፕላኖችን እና ሄሊኮፕተሮችን የታጠቀው የሩሲያ አየር ኃይል በጦር መሳሪያ ብዛት ከዓለም ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።
የሩሲያ አየር ኃይል ከታጠቃቸው አውሮፕላኖች ውስጥ ምዕራባውያን "አስፈሪው ወታደራዊ አውሬ" ብለው የሚጠሩት እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) እንቅልፍ የነሳው ግዙፉ “Tu-160 M2” የጦር አውሮፕላን አንዱ ነው።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል ሀገራት ድንበር ላይ የቆመው እና ኒውክሌር የታጠቀው “አውሬው” የሚል መጠሪያ የተሰጠው አውሮፕላኑ በዓለማችን ላይ ካሉ አደገኛ እና ግዙፍ የጦር አውሮፕላኖች ውስጥ ቀዳሚው ነው።
4 የጄት ሞተሮች የተገጠሙለት በራሪው አውሬ፤ በሰዓት እስከ 2 ሺህ 200 በሚደርስ ፍጥነት ይከንፋል የተባለ ሲሆን፤ በአንድ በረራም እስከ 7 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ የማካለል አቅም አለው ተብሏል።
አውሮፕላኑ ከመሬት እስከ 52 ሺህ ገጫማ ወደላይበመነሳት መብረር ይችላል ተብሏል።
አውሮፕላኑ በጦር አውድማ ላይ እስከ 40 ቶን የሚመዝን ቦምብ በኢላማዎቹ ላይ መጣል እንደሚችልም ተነግሯል።
በክንፉ ላይ 12 ስትራቴጂክ ሚሳዔሎችን መታጠቅ የሚችለው አውሮፕላኑ፤ በሱፐርሶኒክ ፍጥነት የሚጓዙ ሚሳዔሎችን ጭምር በመታጠቅ ጥቃት መፈጸም እንደሚችልም ነው የተነገረው።
በጣም ግዙፍ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ የጦር አውሮፕላን በሶቪየት ህብረት ወቅት ማለትም በፈረንጆቹ 1981 ወደ አገልግሎት የገባ ሲሆን፤ በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት እስካሁን እያገለገለ ይገኛል።