ሩሲያ ለገና በዓል በራሷ ያወጀችው የተኩስ አቁም መገባደዱን አስታወቀች
ሞስኮ ለገና በዓል ያወጀችው የተናጠል ተኩስ አቁም መጠናቀቁን ተከትሎ በጦርነቱ ወደፊት እንደምትቀጥል ቃል ገብታለች
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የጨረሰውና ሚሊዮኖችን ያፈናቀለው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት 11ኛ ወሩ ላይ ነው
ሩሲያ ለገና በዓል ያወጀችው የተናጠል ተኩስ አቁም መጠናቀቁን አስታውቃለች።
ይህንን ተከትሎም ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን በሚገኙ ክልሎች ባደረገችው የቦምብ ጥቃት ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ሞስኮ ራሷ ያወጀችውን የገና በዓል የተናጠል የተኩስ አቁም ካበቃች በኋላ በጎረቤቷ ላይ ድል እስክታገኝ ድረስ በጦርነት ለመቀጠል ቃል ገብታለች።
- የሩሲያው ፕሬዝዳንት በገና በዓል ምክንያት “የተናጠል የተኩስ አቁም” ትእዛዝ አስተላለፉ
- የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ሩሲያ ለገና በዓል ያቀረበችውን የእርቅ ትዕዛዝ “ማደናበሪያ” በሚል ውድቅ አደረጉ
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩስያና የዩክሬን ኦርቶዶክስ ገናን ለማክበር በጦር ግንባሮች ላይ ለ 36 ሰዓታት የሚቆይ ተኩስ አቁም አዘው እንደነበረ ይታወሳል።
ዩክሬን ግን እርምጃውን ማደናበሪያ ነው በሚል ውድቅ አድርጋ የነበረች ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም በትናትናው እለት በአውደ ውጊያዎች ላይ ተኩሶች እንደነበሩም ተነግሯል።
ከበዓሉ እኩለ ሌሊት በኋላ ሞስኮ ጥቃት መጀመሯን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እንደ ሩሲያዊያን አማኞች በፈረንጆቹ ጥር ሰባት የገና በዓልን ያከብራሉ። ነገር ግን በዚህ ዓመት የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ገናን ታህሳስ 25 እንዲከበር መፍቀዱን ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል ዘግቧል።
ሞስኮ በዩክሬን ውስጥ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ብላ የምትጠራውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ገፍታ እንደምትራመድ ተናግራለች።
"በፕሬዝዳንቱ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ የተቀመጡት ተግባራት አሁንም ይሟላሉ" ሲሉ የፑቲን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ሰርጌ ኪሪየንኮ ተናግረዋል። "እናም በእርግጠኝነት ድል ይኖራል" ብለዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለው እና የዩክሬን ከተሞችን ወደ ፍርስራሽነት የለወጠው ጦርነት አሁን በ11ኛው ወሩ ላይ ነው።