ኪቭ፣ ኦዴሳ እና ሌሎች የደቡባዊ ዩክሬን ከተሞች የሩሲያ ሚሳኤል ኢላማዎች ናቸው ተብሏል
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች ከ120 ሚሳኤሎችን ተኮሰች።
ለሁለት ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት 10 ወራት አልፎታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን በመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ዜጎችም ቀላል እንዳልሆነ የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።
ይህ ጦርነት እንዲቆም ብዙዎች ጫና በመፍጠር ላይ ቢሆኑም ሩሲያም ሆነች ዩክሬን ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጣቸው ወደ ድርድር ሊገቡ አልቻሉም።
ዓለም የገና በዓልን እና አዲስ ዓመትን በማክበር ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ሩሲያ በዩክሬን ላይ አዲስ ጥቃት መክፈቷን ሮይተርስ ዘግቧል።
በዛሬው ዕለት ብቻ ሩሲያ ወደ ዩክሬን 120 ሚሳኤል የተኮሰች ሲሆን የሀይል መሰረተ ልማቶች ደግሞ ዋነኛ ኢላማ ሆነዋል ተብሏል።
የዩክሬን የሀይል ሚንስትር ሄርማን ሀሉሽቼንኮ እንዳሉት ኪቭ፣ ኦዴሳ እና ሌሎች የደቡባዊ ዩክሬን ከተሞች በሩሲያ በተተኮሱ ሚሳኤሎች መደብደባቸውን ተናግረዋል።
በዚህ አደጋ ምክንትም 40 በመቶ የኪቭ ከተማ ነዋሪዎች ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ውጪ ሆነዋልም ተብሏል።
በምዕራብ ዩክሬን ካሉት ከተሞች መካከል ትልቋ የምትባለው ልቪቭ ከተማ 90 በመቶ የሀይል መሰረተ ልማት በሩሲያ ጦር እንደወደመ የከተማዋ ከንቲባ ተናግሯል።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ ከሩሲያ ከተተኮሱበት 120 ሚሳኤሎች ውስጥ 16ቱን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በትናንትናው ዕለት ሩሲያ ጦሯን ከክሪሚያ እና በቅርቡ በሀይል ወደ ግዛቷ በህዝበ ውሳኔ ከጠቀለለቻቸው አካባቢዎች ካስወጣች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ሩሲያ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ሰርጊ ላቭሮቭ በኩል ለዩክሬን በሰጠችው ምላሽ ዩክሬን በህዝበ ውሳኔ ወደ ሞስኮ ለተቀላቀሉ ግዛቶች እውቅና ከሰጠች ለድርድር ለመቀመጥ ዝግጁ እንደምትሆን በቅድመ ሁኔታነት ጠቅሳለች።