ጀነራል ሱሮቪኪን ከዋግነር አመጽ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተሰውረው ቆይተዋል
ሩሲያ አዲስ የአየር ሀይል ወታደራዊ አዛዥ ሾመች፡፡
ጀነራል ሰርጊ ሱሮቪኪን የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ አጋር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሲሆን ለረጅም ዓመታትም የሩሲያ አየር ሀይል አዛዥ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ከዓመታት በፊት በሶሰሪያ እየተካሄደ የነበረውን የአይኤስ የሽብር ቡድን ዘመቻ በመምራት ስኬታማ ነበሩ የተባሉት አዛዡ ሀገራቸው በዩክሬን የጀመረችውን ልዩ ዘመቻ መሪም ነበሩ፡፡
በቅጽል ስማቸው ጀነራል አርማጌዶን በመባል የሚታወቁት እኝህ የሩሲያ ጦር መሪ ሞስኮ በዩክሬን የጀመረችው ዘመቻ በታሰበው መልኩ አልሄደም በሚል በጀነራል ጌራሲሞቭ መተካታቸውን ሪያ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ አየር ሀይል አዛዥ ሆነው በመስራት ላይ የነበሩት ጀነራሉ ባሳለፍነው ሀምሌ የዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ከፈጸመው አመጽ ጋር በተያያዘ ከእይታ ርቀው ቆይተዋል፡፡
የዋግነሩ አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዢን ቁልፍ አጋር ናቸው የሚባሉት ጀነራል አርማጌዶን በቤት እስር ውስጥ ቆይተዋል የተባለ ሲሆን የሩሲያ ጦር ስለጉዳዩ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ጀነራል አርማጌዶን በሩሲያ ጦር ውስጥ ይቆያሉ የተባለ ሲሆን አሁን ላይ በእረፍት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ጀነራል አርማጌዶን ተክተው የሩሲያ አየር ሀይል አዛዥ የተደረጉት ጀነራል ቪክተር አፍዛሎቭ በዚያው በሀገሪቱ አየር ሀይል ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ የጦር መሪ እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በሩሲያ ጦር ላይ በማመጽ እና በሀገር ክህደት ተከሰው የነበሩት የዋግነር ጦር አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዢን ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በተደረገ ድርድር ክሱ ተቋርጦ ወደ ቤላሩስ እንዲኮበልሉ ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡
አዛዡ ለጥቂት ቀናት ወደ ቤላሩስ ቢኮበልሉም ዳግም ወደ ሩሲያ በመመለስ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ አሁንም የዋግነር ጦርን በመምራት ላይ ናቸው፡፡
በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ያወደሱት ፕሪጎዢን ከሰሞኑ ደግሞ አፍሪካን ነጻ እያወጡ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መፈንቅለ መንግስት በተደጋጋሚ በመፈጸም ላይ ሲሆን ስልጣን በሀይል የተቆጣጠሩ ወታደራዊ መሪዎች ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡