ሩሲያ እየሰራችው ነው የተባለው የህዋ ላይ ኑክሌር ጦር መሳሪያ ምን አይነት ባህሪ አለው?
አሜሪካ ሩሲያ በህዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶችን መምታት የሚያስችል ኑክሌር ጦር መሳሪያ እየሰራች ነው ስትል ከሳለች
ሩሲያ በበኩሏ ወደ ህዋ ቁሳቁሶችን ያጓጓዝኩት ሳተላይቶቼን ለማደስ እንጂ ሌላ ዓላማ የለኝም ብላለች
ሩሲያ እየሰራችው ነው የተባለው የህዋ ላይ ኑክሌር ጦር መሳሪያ ምን አይነት ባህሪ አለው?
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ ሩሲያ በህዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶችን ስራ የሚያውክ ኑክሌር ጦር መሳሪያ እየሰራች ነው ብላለች፡፡
የሩሲያ ድርጊት በአሜሪካ ለሚመራው የዓለማችን ስርዓት ዋነኛ እንቅፋት ይሆናል የተባለ ሲሆን ዋሸንግተን ዋነኛ የደህንነት ችግር እንደገጠማት ከሰሞኑ አስታውቃ ነበር፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት አሜሪካ ከባድ የደህንነት ችግር ገጥሟታል፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስለሚወስዱት እርምጃ ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል ሲሉም አሳስቦ ነበር፡፡
ዘግይቶ በወጣ ተጨማሪ መረጃ መሰረት አሜሪካ ብርቱ የደህንነት ችግር የገጠማት ሩሲያ በህዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶችን መምታት የሚያስችል የኑክሌር ጦር መሳሪያ እየሰራች ነው በሚል ነው፡፡
እንደ ዋሸንግተን ገለጻ ሩሲያ እየሰራችው ያለው ኑክሌር መሳሪያ ሲተኮስ በህዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶች የሀይል ማዕበል እንዲፈጠር በማድረግ የግል እና መንግስታዊ ሳተላይቶችን ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ ነው፡፡
እነዚህ ሳተላይቶች በሩሲያ ሰራሹ ኑክሌር መሳሪያ ከጥቅም ውጪ ከሆኑ ኢንተርኔት፣ የሞባይል ስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲቆሙ እና ዓለምን ከግንኙነት ውጪ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
ወታደራዊ የሳተላይት ባለሙያዎች በበኩላቸው ሩሲያ ልትሰራው ያሰበችው የጦር መሳሪያ ኑክሌር ኤሌክትሮ ማግኔቲክ የሚባል እና በመሬት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ሌሎች ሳተላይቶች ወደ መሬት እንዲወርዱ የማድረግ ሀይል ያለው ነው ብለዋል፡፡
ባለሙያዎቹ አክለውም ዩክሬን እየተጠቀመችባቸው ያሉ እንደ ስታርሊንክ አይነት ሳተላይቶችን ለይቶ ለመምታት ልትጠቀምበት ትችላለችም ተብሏል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ በአሜሪካ የቀረበባትን ክስ ውድቅ ያደረገች ሲሆን ወደ ህዋ እያጓጓዝኩት ያለው ቁሳቁስም ሳተላይቶቼን ለማደስ ነው በሚል አስተባብላለች፡፡