በዩክሬን ሰላም አስከባሪ ጦር በማሰማራት ጉዳይ ውሳኔ ሰጪዋ ሩሲያ አይደለችም - ማክሮን
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት "ዩክሬን ሉአላዊ ሀገር ናት፤ የአንድነት ሃይሎች በግዛቷ እንዲሰማሩ ከጠየቀች የሞስኮ ድጋፍ አይጠበቅም" ብለዋል

ፈረንሳይ እና ብሪታንያ ለዩክሬን ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
በዩክሬን ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በማሰማራት ጉዳይ ሩሲያ ውሳኔ የመስጠት ድርሻ እንደማይኖራት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታመር እና ሌሎች መሪዎች ጋር ለዩክሬን በሚደረግ ድጋፍ ዙሪያ በበይነ መረብ መክረዋል።
ማክሮን ከምክክሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ዩክሬን ሉአላዊ ሀገር ናት፤ የአንድነት ሃይሎች በግዛቷ እንዲሰማሩ ጥያቄ ካቀረበች ሩሲያ የምትቀበለው ወይ ውድቅ የምታደርገው ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።
ሩሲያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋሮች ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በዩክሬን የማሰማራት እቅድን በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጓን ሬውተርስ አስታውሷል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በነጩ ቤተመንግስት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፊት ከተነሱ በኋላ የፈረንሳይ እና ብሪታንያ መሪዎች የሰላም አስከባሪዎች ስምሪት እቅዱን ጎላ አድርገው ሲያቀርቡት ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን የሰላም አስከባሪ ሃይሉ "ከእያንዳንዱ ሀገር የሚውጣጣ እና በጥቂት ሺዎች የሚቆጠር ነው" ያሉ ሲሆን፥ በየወሰኑ ወሳኝ ስፍራዎች እንደሚሰማራም ተናግረዋል።
የአውሮፓ ሀገራት ብቻም ሳይሆኑ ሌሎች የኬቭ አጋሮች ወታደሮቻቸውን ለመላክ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም ዝርዝር ማብራሪያን ግን አልሰጡም።
ፊንላንድ እና አውስትራሊያ በሰላም አስከባሪ ሃይል ስምሪቱ ዙሪያ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሃሙስ ዋሽንግተን ያቀረበችውን የ30 ቀናት ተኩስ አቁም ምክረሃሳብ በመርህ ደረጃ መቀበላቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እስኪደረስ ግን ጦርነቱ ይቀጥላል ማለታቸው አይዘነጋም።
የሩሲያ ጦር ባለፈው አመት ነሃሴ ወር ላይ የሀገሪቱን ድንበር ጥሰው የገቡ የዩክሬን ወታደሮችን ሙሉ በሙሉ ለማስወጣት የጀመረው ውጊያ መቀጠሉ ተሰምቷል።
ኬቭ በበኩሏ በኩርስክ ክልል የሚገኘው የዩክሬን ጦር "ተከቧል" በሚል ሞስኮ ያወጣችውን መረጃ ሀሰተኛ ነው በማለት አስተባብላለች።