ፑቲን የዩክሬን ወታደሮችን ሙሉ በሙሉ ከሩሲያ ግዛት ማስወጣት እንደሚገባ አሳሰቡ
ፕሬዝዳንቱ በኩርስክ ያልተጠበቀ ጉብኝት ባደረጉ ማግስት የሩሲያ ጦር ቁልፍ ከተማ የሆነችውን ሱድዛ ዳግም መቆጣጠሩ ተገልጿል

ዩክሬን በነሃሴ ወር ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ በመግባት የተቆጣጠረችውን ኩርስክ ዋነኛ የመደራደሪያ ካርድ ለማድረግ አቅዳ ነበር
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ወታደሮች ተይዛ የቆየችውን ሱድዛ ከተማ ዳግም መቆጣጠሩ ተነገረ።
"ሜሎቪ እና ፓዶል የተሰኙ መንደሮችም ነጻ ወጥተዋል" ብሏል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ።
ሩሲያ በኩርስክ ክልል ትልቅ የሆነችውን ሱድዛ የተቆጣጠረው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በኩርስክ ያልተጠበቀ ጉብኝት ባደረጉ ማግስት ነው።
ሞስኮ የአሜሪካ እና ዩክሬን ባለስልጣናት በጂዳ ባደረጉት ምክክር የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ስምምነቱ ሳይጀመር የዩክሬንን ጦር ሙሉ በሙሉ ከግዛቷ ለማስወጣት ጥድፊያ ላይ መሆኗ ተገልጿል።
የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሃሳቡ ዙሪያ ገለጻ ለማድረግ ዛሬ ሞስኮ መግባታቸውን ታስ የዜና ወኪል አስነብቧል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ፕሬዝዳንት ፑቲን የኩርስክ ክልል በፍጥነት ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣት እንዳለበት አሳስበዋል፤ የወታደሮቻችን እና ንጹሃንን እልቂት ለመቀነስ የምናደርገው ጥረት ጊዜ ቢወስድም ኩርስክ በአጭር ጊዜ ነጻ መውጣቷ አያጠያይቅም" ብለዋል።
የፑቲን የኩርስክ ጉብኝት ባለፈው አመት ወደ ሩሲያ የገባውን የዩክሬን ጦር ጠራርጎ ለማስወጣት እየታገሉ የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮችን ሞራል ለማነቃቃት ያለመ መሆኑን ሲኤንኤን አስነብቧል።
ኬቭ በነሃሴ ወር 2024 የሩሲያዋን ኩርስክ ክልል የተቆጣጠረችው ከሞስኮ ጋር ለምታደርገው የተኩስ አቁም ንግግር እንደ መደራደሪያ እንዲሆናት በማሰብ ነበር።
"በኩርስክ ክልል የሚያዙ የዩክሬን ወታደሮች እንደ ሽብርተኛ ይቆጠራሉ" ያሉት ፑቲን በትናንቱ ጉብኝታቸው ኬቭ ምንም አይነት የመደራደሪያ ካርድ እንዳይኖራት አሳስበዋል ነው የተባለው።
የዩክሬን ጦር አዛዥ ጀነራል ኦሌክሳንደር ሲይርስኪ በበኩላቸው "የዩክሬን ወታደሮችን ህይወት መታደግ" ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ጦራቸው እያፈገፈገ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪም ሞስኮ በኩርስክ ክልል ከባድ ጥቃት እየፈጸመች መሆኑን በመጥቀስ የጀነራል ሲይርስኪን ሃሳብ አጠናክረዋል።
የሩሲያ ጦር ከፍተኛ ጀነራል ቫለሪ ገራሲሞቭ የሀገራቸው ጦር 86 በመቶ የሚሆነውን የኩርስክ ክልል ነጻ ማድረጉንና 430 የዩክሬን ወታደሮችን በምርኮ መያዙን ገልጸዋል።