ዩክሬን ከተቆጣጠረችው የከርስክ ግዛት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እየለቀቀች እንደምትገኝ ተገለጸ
ሩስያ በዛሬው ዕለት በግዛቱ ተጨማሪ አምስት መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታውቃለች

በሁለቱም ወገን የሚወጡ መረጃዎች እስከ መጪው አርብ ድረስ የዩክሬን ጦር ከስፍራው ሙሉ ለሙሉ ሊለቅ እንደሚችል አመላክተዋል
ዩክሬን ባለፈው ነሀሴ ወር በምዕራብ ሩስያ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ተቆጣጥራው ከነበረው የከርስክ ግዛት በስፋት እየለቀቀች አንድምትገኝ ተዘግቧል፡፡
ግዛቱን ለማስለቀቅ የሩስያ ጦር በግስጋሴው ሲቀጥል የዩክሬን ወታደሮች በበኩላቸው በከባድ ውጊያ የተቆጣጠሯቸውን ጠንካራ ይዞታዎች ለቀው እየወጡ እንደሚገኝ ነው የተነገረው፡፡
ኪየቭ ባልተጠበቀ ጥቃት ተቆጣጥራው የነበረው የኩስሰክ ግዛት የወታደሮቿን የውጊያ ሞራል ከመጨመሩ ባለፈ በጦርነቱ የመደራደር አቅሟን አሳድጎት እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
ነገርግን ከ7 ወራት ከባድ ውጊያ በኋላ የዩክሬን ይዞታዎች ቀስ በቀስ እየቀነሱ ሲመጡ ሩስያ በበኩሏ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በርካታ ስፍራዎችን ድጋሚ መቆጣጠር ችላለች፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በግዛቱ ተጨማሪ አምስት መንደሮች መያዙን አስታውቋል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው የውጊያ ውሎዎች ተለዋዋጭነት ለሩስያ ማድላታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ በዘገባው በሩሲያ ጦማሪዎች እና በመንግስት ሚዲያዎች የተጋራውን የግዛት ማስለቀቅ የሚያሳይ ቪዲዮ ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሷል፡፡
በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው እና ዩክሬን ለሎጂስቲክስ ማስተላለፊያ በምትጠቀምበት ሱድዛ በተባለው ስትራቴጂያዊ አካባቢ የሩስያ ወታደሮች የሀገሪቱን ባንዲራ ሲስቅሉ በቪድዮው ላይ ታይቷል፡፡
የዩክሬን ከፍተኛ አዛዥ በዚህ ሳምንት ወታደሮቻቸው በኩርስክ ግዛት እየተከበቡ እንደሚገኙ ለተሰራጨው ዘገባ በሰጡት ማስተባበያ “የተሻለ የመከላከል ስፍራን ለመያዝ ነው የለቀቅነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ስካዶቭስኪ ዲፌንደር” የተሰኘው የዩክሬን ወታደራዊ ጦማሪ በቴሌግራም ገጹ ላይ ባሰራጨው መረጃ "የዩክሬን ጦር ኃይሎች ኩርስክን ለቀው እየወጡ ነው፤ እስከ አርብ ድረስ ምንም የዩክሬን ወታደር በስፍራው አይኖርም" ብሏል፡፡
ሩስያዊው ገለልተኛ የፖለቲካ ተንታኝ ሩስላን ሌቪቭ በበኩሉ “የዩክሬን ጦር ለተጨማሪ ሁለት ቀናት በግዛቱ ለመቆየት ሊዋጋ ይችላል ፤ ነገር ግን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ የኩርሰክ ግዛት ወረራ በጣም በአጭር ቀን ሙሉ ለሙሉ ይቀለበሳል” ሲል ተናግሯል፡፡