ሩሲያ በዩክሬኗ ኬርሰን ግዛት ለማካሄድ አቅዳ የነበረውን ህዝበ ውሳኔ አዘገየች
ህዝበ ውሳኔው ሊቆይ የቻለው “እየተከሰቱ ባሉት ሁነቶች ምክንያት ነው” ተብሏል
የዩክሬን ግዛቶች የሆኑት ሉሃንስክና ዶንባስ ግዛቶች በሩሲያና አጋሮቿ የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና እንደተሰጣቸው ይታወሳል
ሩሲያ በቁጥጥሯ ስር ባለችው የዩክሬን ኬርሰን ግዛት ለማካሄድ አቅዳ የነበረውን “ህዝበ ውሳኔ ለጊዜው ማቆየቷን” ኪሪል ስትሬሞሶቭ የተባሉ ከፍተኛ የሩሲያ ባለስልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኪሪል ስትሬሞሶቭ ለሩሲያ 1 ቲቪ ቻነል በሰጡት አስተያየት “ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል፣ በቅርቡ ህዝበ ውሳኔ ለማድረግም ፈልገን ነበር፣ነገር ግን እየተከሰቱ ባሉት ሁነቶች ምክንያት ህዝብ ውሳኔው የምናቆየው ይመስለኛል” ብለዋል።
የክሬምሊን ባለስልጣናት፤ በያዝነው ወርሃ ነሃሴ የሩሲያ ጦር የተቆጣጠራቸው የዩክሬን ግዛቶች በተለይም በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት አካባቢዎች ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂዱ መሆኑ ከሁለት ወራት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር የሚገኙት የደቡብ ዩክሬኖን ግዛቶቹ ዛፖሪዢያ እና ኬርሰን ህዝብ ውሳኔ ይካሄድባቸዋል ከተባሉት አከባቢዎች እንደነበሩም አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የዩክሬን ግዛቶች የሆኑት ሉሃንስክ እና ዶንባስ ግዛቶች በሩሲያ፣ ሶሪያ እና ሰሜን ኮሪያ የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና አግኝተዋል።
ያም ሆኖ ዩክሬን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ድርጊቱን ኮንነዋል።
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያቀል አዲስ አዋጅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
አዋጁ በሩሲያ ጦር እና በደጋፊዎቹ ቁጥጥር ስር በዋሉ የዩክሬን ግዛቶች ለሚገኙ ዜጎች የተፋጠነ ፓስፖርት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው።
ፑቲን የፈረሙት አዲሱ አዋጅ አዲሱ አዋጅ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት የዛፖሪዢያ እና ኬርሰን አካባቢ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል መባሉንም ነው ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው።
ሆኖም እርምጃውን የተቃወሙ የኪቭ ባለስልጣናት አዋጁ ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ አሳስበዋል።
እርምጃው የዩክሬንን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት የሚጥስ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የሚጥስ እንደሆነም ነበር ባለስልጣናቱ የገለጹት።