የሩሲያ ጦር የተቆጣጠራቸው የዩክሬን ግዛቶች ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂዱ ነው
የደቡባዊ ዩክሬን ግዛቶች ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል የፊታችን መስከረም ህዝበ ውሳኔ እናካሂዳለን ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ለሁሉም ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ ማውጣታቸው ይታወሳል
የሩሲያ ጦር የተቆጣጠራቸው የዩክሬን ግዛቶች ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂዱ ነው።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከተጀመረ 142ኛ ቀኑ ላይ የደረሰ ሲሆን እስካሁን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ተሰደዋል።
ሉሃንስክ እና ዶንባስ ግዛቶችን ጨምሮ በርካታ የዩክሬን ግዛቶች በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር የወደቁ ሲሆን፤ ዩክሬን የሩሲያን ድርጊት አውግዛ ግዛቶቿን ለማስመለስ እስከመጨረሻው እንደምትዋጋ አስታውቃለች።
በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት አካባቢዎች ደግሞ ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ከሁለት ወር በኋላ ህዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂዱ ተገልጿል።
የዛፖሪዚያ ግዛት በመባል የሚታወቀው የዩክሬን ግዛት አሁን ላይ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፤ ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሆነ ሮቶይተርስ ዘግቧል።
የዩክሬን ግዛቶች የሆኑት ሉሃንስክ እና ዶንባስ ግዛቶች በሩሲያ፣ ሶሪያ እና ሰሜን ኮሪያ የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ ዩክሬን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ድርጊቱን ኮንነዋል።
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያቀል አዲስ አዋጅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
አዋጁ በሩሲያ ጦር እና በደጋፊዎቹ ቁጥጥር ስር በዋሉ የዩክሬን ግዛቶች ለሚገኙ ዜጎች የተፋጠነ ፓስፖርት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው።
ፑቲን የፈረሙት አዲሱ አዋጅ አዲሱ አዋጅ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት የዛፖሪዢያ እና ኬርሰን አካባቢ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል መባሉን ነው ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው።
ሆኖም እርምጃውን የተቃወሙ የኪቭ ባለስልጣናት አዋጁ ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ አሳስበዋል።
እርምጃው የዩክሬንን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት የሚጥስ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የሚጥስ እንደሆነም ነው ባለስልጣናቱ የገለጹት።