ጠቅላላ ጉባዔው በእነ አሜሪካ የተጠራ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያን ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለማስወጣት ነገ ሃሙስ ድምጽ ይሰጣል፡፡
ድምጹ የሚሰጠው ሩሲያ ዩክሬንን በመውረር ለፈጸመችው ጥፋት ለመቅጣት እንደሆነ የጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡ ሃሙስ 4፡00 ላይ ድምጽ እንደሚሰጥም የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡
ድምጽ የሚሰጠው ሩሲያን ከምክር ቤቱ ለማስወጣት በዛቱት በምዕራባውያን ሃገራት ጥያቄ ነው፡፡
በተለይም ከሰሞኑ ቡቻ በተባለው የኪቭ አካባቢ በርካታ ዩክሬናውያን ንጹሃን በሩሲያ ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል መባሉን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቿ ጠቅላላ ጉባዔው ሩሲያን እንዲያስወጣ ጠይቀዋል፡፡ 50 ንጹሃን ተገድለዋል መባሉን ተከትሎም ከፍተኛ ግፊት ተደርጓል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው ከአባል ሃገራቱ የተውጣጡ 193 አባላት አሉት፡፡ ከ193ቱ ሁለት ሶስተኛው ሃሳቡን ከደገፉ ሩሲያ ከአባልነት የምትሰናበት ይሆናል፡፡
የሩሲያ በምክር ቤቱ አባልነት መቀጠል ስላቅ ነው ሲሉም ነበር በተመድ የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ከሰሞኑ ለምክር ቤቱ ስለሁኔታው የገለጹት፡፡ ይህ መሆኑ ስህተት እንደሆነ በማሳሰብም ሩሲያ መቀመጫውን ኒውዮርክ ካደረገው ተቋም እንድትሰናበት ጠይቀዋል፡፡
በምክር ቤቱ ለሩሲያ የሚሆን ቦታ ሊኖር አይገባም ያለችው ዩክሬንም የፈጸመችውን ወንጀል ለማጋለጥ የሚያስችሉ መረጃዎችን አሰባስቤ አቀርባለሁ ብላለች፡፡
በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫዚሊ ንቤዢያ የማይታመን ሲሉ ስለ ሁኔታው ብስጭታቸውን ገልጸዋል ለሰላም ሂደቶች እንደማይጠቅም በመጠቆም፡፡ ሃገራቸው ተቀናብሮ የቀረበ ነው ስላሉት የቡቻ ጅምላ ግድያ መረጃዎችን እንደምታቀርብም ነው አምባሳደር ቫዚሊ የተናገሩት፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከአሁን ቀደምም ከዩክሬን ወረራ ጋር በተያያዘ በሩሲያ ላይ ምርመራዎችን ለመጀመር የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ በኪቭ ጠያቂነት አቅርቦ ነበር፡፡
ሆኖም 32 አባል ሃገራት የውሳኔ ሃሳቡን ቢደግፉም ራሷ ሩሲያ እና ኤርትራ ተቃውመዋል፡፡ ቻይናን ጨምሮ 13 ሀገራት ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦን መርጠዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው ካሁን ቀደም በፈረንጆቹ መጋቢት 2011 በእንዲህ ዐይነት የድምጽ አካሄድ ሊቢያን ከምክር ቤቱ ውጭ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡