ፖለቲካ
ሱዳንን ያካተተው የአረብ ሃገራት ልዑክ ሩሲያ እና ዩክሬንን ማሸማገል እፈልጋለሁ አለ
ልዑካኑ በፖላንድ ከዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ይወያያሉ ተብሏል
ከአረብ ሊግ አባል ሃገራት የተውጣጡ ልዑካን በሞስኮው ጉብኝት አድርገዋል
የአረብ ሃገራት ሩሲያ እና ዩክሬንን ለመሸምገል እንፈልጋለን አሉ፡፡
ከአረብ ሊግ አባል ሃገራት የተውጣጡ ልዑካን ትናንት ሰኞ በሩሲያ ሞስኮው ጉብኝት አድርገው ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡
የግብጽ፣ የአልጄሪያ፣ የኢራቅ፣ የዮርዳኖስ እና የሱዳን ባለስልጣናት ናቸው በልዑኩ የተካተቱት፡፡ የአረብ ሊግ ዋና ጸሃፊ መሃመድ አቡል ጌይትን ያካተተው ልዑክ ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ተወያይቷል፡፡
ከውይይቱ በኋላ መግለጫ የሰጡት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ለማሸማገል ያለንን ፍላጎት አሳውቀናል ብለዋል፡፡
ሹክሪ በልዑኩ ከተካተቱ የአረብ ሊግ ባለስልጣናት መካከል ናቸው፡፡
ሊጉ እንዳስታወቀው ከሆነ ልዑካኑ ከዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር ለመወያየት ወደ ፖላንድ ያቀናሉ፡፡