ከ10 ወር በፊት የተጀመረው ይህ ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በገዳይነቱ ወደር የለውም ተብሏል
ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን ጉዳይ ላይ ለመደራደር ዝግጁ ናት አሉ
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከተሳተፉት ሁሉም ወገኖች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
ፑቲን እሁድ እለት በተለቀቀ ቃለ ምልልስ ሆኖም ኪየቭ እና ምዕራባውያን ደጋፊዎቿ ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው የካቲት ወር የተቀሰቀሰው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ እጅግ ገዳይ የተባለ ግጭት ሲሆን፤ እ.አ.አ ከ1962ቱ የኩባ ሚሳይል ቀውስ በኋላ በሞስኮ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ትልቁ ግጭት ነው።
እስካሁን ድረስ ለጦርነቱ መጨረሻ ያልተገኘለት ሲሆን፤ ክሬምሊን ዓላማዬ ሁሉ እስኪሳካ ድረስ እዋጋለሁ ብሏል። ኪየቭ ደግሞ እያንዳንዱ የሩስያ ወታደር ከግዛቱ እስካልተባረረ ድረስ አላርፍም ሲል፤ ሩሲያን በፈረንጆቹ 2014 የተቀላቀለችውን ክሪሚያን ጨምሮ አስመልሳለሁ ብሏል።
ፑቲን በቃለ ምልልሱ ለሩሲያ የመንግስት ቴሌቪዥን እንደተናገሩት "ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር ተቀባይነት ስላላቸው መፍትሄዎች ለመደራደር ዝግጁ ነን፣ ነገር ግን በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጡ የነሱ ጉዳይ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ለመደራደር ፈቃደኛ ያልሆኑት እኛ ሳንሆን እነሱ ናቸው" ብለዋል።
የአሜራካ የስለላ ተቋም የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊልያም በርንስ በዚህ ወር በታተመት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት አብዛኞቹ ግጭቶች በድርድር የሚያበቁ ቢሆንም የሲአይኤ ግምገማ ግን ሩሲያ ጦርነቱን ለማቆም እውነተኛ ድርድር ለማድረግ ፍላጎት የላትም።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አማካሪ ፑቲን ወደ እውነታው መመለስ እና ምንም አይነት ድርድር የማትፈልገው ሩሲያ መሆኗን አምነው መቀበል አለባቸው ብለዋል።
"ሩሲያ ድርድርን አትፈልግም። ነገር ግን ኃላፊነትን ለማስወገድ ትጥራለች" ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።