የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የዓለምን የፖለቲካ አሰላለፍ እና የኃይል ሚዛን እየቀየረ ይሆን?
ኤሚሬቶች ወደየትኛውም ኃያል ሀገር ከማዘንበል ይልቅ ገለልተኛ አካሄድን መምረጣቸው ተነግሯል
ዐረብ ኢሚሬቶች ፣ ሕንድና ቻይና በሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይ ለምን ድምጸ ተአቅቦ አደረጉ?
ዓለም ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት ላለማየት በየዕምነቱ እየጸለየ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ ሩሲያ እና ዩክሬን ከአምስት ቀናት በፊት የጀመሩት ጦርነት የብዙዎችን ህይወት ሲቀጥፍ በርካቶችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፡፡
ሞስኮ እና ኪቭ ከአምስት ቀናት በኋላ ዛሬ በቤላሩስ የሰላም ንግግር መጀመራቸው ቢነገርም የወታደሮቻቸው ጠብመንጃ ግን አልተዘቀዘቀም፡፡ ሩሲያ በርካታ የፋይናንስ እና የበረራ ማዕቀቦች ቢጣሉባትም ዘመቻውን ግን በይፋ እያስኬደችው ነው፡፡
ይህን ጨምሮ የምዕራባውያንን ማዕቀብ ማዥጎድጎድ ተመልከተውም ይመስላል የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የምዕራባውያን ማዕቀቦችን “ሩሲያን ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እየገፋት ነው” ያሉት፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት እዛው የሚቀር ሳይሆን ዓለምን ያነጋገረና ገና የሚያነጋግር እንደሚሆን እየታየ ነው፡፡ የዚህ ማሳያው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በአስቸኳይ ሲነጋገርበት የደገፉ፣ የተቃወሙ እንዲሁም ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ሀገራት አሉ፡፡ ቻይና፣ ሕንድና የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች (ዩኤኢ) ድምጸ ተዓቅቦን የመረጡ ሃገራት ናቸው፡፡ ይህም በጦርነቱ ምክንያት ዓለም ወዴት እየሄደች ነው? በዓለም የፖለቲካ አሰላለፍና ሚዛን ላይስ ለውጦች እየመጡ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን በብዙዎች ዘንድ አጭሯል፡፡
ሁኔታው ምንም እንኳን አቅማቸው ቢለያይም ኃያል ሃገራት እየተፈጠሩ መሆኑን (multipolar) የሚያሳይ ነው የሚሉት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አለሙ አስፋው የኃይል ሚዛኑን የሚቀይር ሁኔታ መፈጠሩንም የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የቻይና ፣ ህንድ ወይም የዩኤኢ መታቀብ ይህንኑ እንደሚያሳይም ነው የገለጹት፡፡ ሀገራቱ ከማንም ጋር ባለመወገን የራሳቸውን ጥቅም በማስላት መሃል ላይ መቆም እንደሚቻል ያሳያሉ ብለዋል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሙሉቀን ይታይህ በበኩላቸው ሃገራቱ የታቀቡት የትኛውንም ወገን ላለማስቀየም ወይም ፖለቲካዊ ሁኔታን በማገናዘብ ነው ይላሉ፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን በማሳያነት የሚያነሱት መምህር አለሙ አስፋውም ቢሆኑ ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ አቡዳቢ ይህን ማድረጓ ከየትኛውም ጎን አለመቆሟንና የራሷን ጥቅም በማሰብ በገለልተኛነት መንቀሳቀስ መጀመሯን ያመለክታል እንደ መምህሩ ገለጻ፡፡
አሁን ላይ ዩኤኢ ራሷን ችላ እንደ አንድ ዋነኛ ኃይል እየወጣች መሆኑን የሚያነሱት መምህሩ ኤሚሬት በየትኛውም ሃያል ሀገር ጥላ ስር ከመሆን ይልቅ የራስን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ ትኩረት አድርጋለች ሲሉ ነው የሚያስቀምጡት፡፡