ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ለድንገተኛ ጊዜ ብቻ እንደምትጠቀም አስታወቀች
ከኔቶ እና አሜሪካ ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት እንደሌላትም ሩሲያ ገልጻለች
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 176ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ለድንገተኛ ጊዜ ብቻ እንደምትጠቀም አስታወቀች፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሩሲያ የኑክሌር መሳሪያዎቿን ለድንገተኛ ሁኔታዎች ብቻ እንደምትጠቀማቸው አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ አክሎም ሩሲያ ከሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ እና አሜሪካ ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት እንደሌላት አስታውቋል፡፡ ሩሲያ በዩክሬን ምድር እያካሄደች ባለችው ልዩ ዘመቻ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን የመጠቀም ፍላጎት እና እቅድ እንደሌላትም ገልጻለች፡፡
በመሆኑም ሩሲያ በዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን እያስጠጋች እንደሆነ ተደርጎ የሚሰራጩ መረጃዎች እና ዘገባዎች ሀሰት መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡
በመሆኑም ሩሲያ የኑክሌር የጦር መሳሪያዎችን የምትጠቀመው ለመልሶ ማጥቃት ብቻ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ጠቁማለች፡፡
እንዲሁም በሩሲያዊያ ላይ አውዳሚ የጥቃት አደጋ ሲጋረጥ፣ እንደ ሀገር ህልውና ላይ አደጋዎች ሲያጋጥሙ አልያም በዚህ ልክ አስከፊ አደጋዎች የመድረስ እድሎች ሲያጋጥሙ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን እንደምትጠቀም ተጠቅሷል፡፡
በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር ሩሲያ እና አሜሪካ ወደ ቀጥታ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
እንደ ሩሲያ ቱዴይ ዘገባ ከሆነ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት የያዘችበት መንገድ ሀላፊነት የጎደለው፣ ለጦርነት ጥቂት ነገሮች የቀሩበት ደረጃ ላይ መድረሱን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሩሲያ እና አሜሪካ ግንኙነት የማይገመት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚናገሩት አምባሳደሩ የኑክሌር ጦርነት ሊጀምሩ እንደሚችሉም ስጋታቸውን ጠቁመውም ነበር።