የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ሰራተኞች በአሳማ ጉንፋን መያዛቸው ተገለጸ
ጉንፋኑ በሩሲያ 74 ግዛቶች ውስጥ በስፋት እየተስፋፋ ተብሏል
የሩሲያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሩሲያውያን የመከላከያ ክትባቶችን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ሰራተኞች በአሳማ ጉንፋን (ስዋይን ፍሉ) መያዛቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ገለጹ፡፡
ጉናፋኑ በመላው ሩሲያ በስፋት እየተስፋፋ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ የሩስያ ዜጎች በቫይረሱ እንዳይያዙ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ጭንብል መልበስ እና ክትባት መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጉንፋኑ በሩሲያ 74 ግዛቶች ውስጥ እየተስፋፋ ነው ያሉት የሩሲያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሚካሂል ሙራሽኮ በበኩላቸው ሩሲያውያን የመከላከያ ክትባቶችን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሳማ ጉንፋን በአሳማዎች ውስጥ በጀመረ የኤች 1 ኤን 1 ቫይረስ ዝርያ ምክንያት የሚከሰት የሰው የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ነው።
የስዋይን ፍሉ ወረርሺኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው እንደፈረንጆቹ 1919 ሲሆን በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰት ነው፡፡
የጉንፋኑ ምልክቶቹ ትኩሳት፣ ሳል፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ ብርድ ብርድ ማለት እና የሰውነት ህመም ናቸው።
እረፍት ፣ የህመም ማስታገሻዎችን እና ፈሳሾችን መውሰድ ከበሽታው ለመዳን የሚጠቅሙ የተለመዱ የማገገምያ መንገዶች ናቸው፡፡